በአማራ ክልል የሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን የመከላከል ጥምረት ተመሠረተ።

29

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 8/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን የመከላከል ጥምረት ከአጋር አካላት ጋር መሥርቷል። ጥምረቱ የተመሠረተው ከአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከሙያ ማኅበራት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ነው።

በምሥረታ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሲቪክ ማኅበራት ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ በሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን በመከላከል ሥራዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃብታሙ ሞገስ ኮሚሽኑ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ፣ የተቋም የአሠራር ሥርዓት ጥራት፣ የሙስና መከላከል እና የሃብት ምዝገባ በሕግ የተሰጡት ተግባራት መኾናቸውን ገልጸዋል። ክልሉ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ኾኖ የተለያዩ ተግባራትን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር መፈጸሙን ጠቅሰዋል። የተሠራው ሥራ ግን በቂ አለመኾኑን ነው ያመላከቱት። ለሥነ ምግባር ግንባታ እና ለሙስና መከላከል ትኩረት በማድረግ ከክልሉ ምክር ቤት ጋር በመነጋገር እና በመቀናጀት ለመሥራት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከሰሜኑ ጦርነት ማግስት በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመቀነስ እንቅፋት መፈጠሩን ገልጸዋል። ባለው ችግር ምክንያት የሚፈለገው ውጤት አለመገኘቱንም አመላክተዋል።

ችግሩን ከመሠረቱ ካልፈታን ተባብሶ ይቀጥላል ያሉት ኮሚሽነሩ የሥነ ምግባር ግንባታ እና የሙስና መከላከሉን ተግባራት ተባብሮ ለመሥራት ጥምረት መመሥረት አስፈላጊ ነው ብለዋል። የጥምረቱ ዓላማዎች ሁሉም ተቋማት ሠራተኞቻቸውን በሥነ ምግባር በመገንባት፣ ከብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት፣ በሥነ ምግባር ግንባታ እና በጸረ ሙስና ትግሉ ተቋማት ተቀናጅተው የሚሠሩበትን አሠራር በማበጀት ለመነጋገር መኾኑን ገልጸዋል።

የሚዲያ አካላት ለትግሉ ያላቸውን ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ ለውጤታማ ሥራ የበኩላቸውን እንዲወጡም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተሻሻለው የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ፀደቀ።
Next articleሕዝቡ የሰጣቸውን አደራ ለመወጣት እየሠሩ እንደሚገኙ በኦሮሚያ ክልል በአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ ላይ እየተሳተፉ ያሉ የኅብረተሰብ ተዎካዮች ገለጹ።