
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ነው የብሔራዊ ባንክ አዋጅን ያፀደቀው፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ የምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ አዋጁ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተረጋጋ ሆኖና ጥራቱን ጠብቆ እንዲሄድ ያስችላል ብለዋል፡፡
አዋጁ የባንኩን ዓላማ በግልጽ እንዳስቀመጠ ገልጸው የባንኩ ዋና ሥራ በኢትዮጵያ የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር ማስቻልና የፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም በኢትዮጵያ ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽዖ ማድረግ የባንኩ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አዋጁ ባንኩ እንዲዘምንና በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ከሚኖሩ ለውጦች ጋር እንዲጣጣም እንዲሁም የቁጥጥር አቅሙን እንዲያጎለብት ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡
የባንኩን አደረጃጀት፣ ዓላማና ተግባር፣ ስለ ብሔራዊ ባንክ አሥተዳደር፣ ባንኩ ከመንግሥትና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነትና ሌሎችንም ድንጋጌዎች አዋጁ ማካተቱን አብራርተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!