በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳድር ያሉ ጸጋዎችን መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ።

26

ሰቆጣ፡ ታኅሣሥ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት ዋግኽምራ ያሏትን ጸጋዎች በአግባቡ እንድትጠቀም ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ በሰቆጣ ከተማ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የተገኙት የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ከተከዜ ሰው ሠራሽ ሐይቅ እስከ 10 ሽህ ቶን የዓሳ ምርት፣ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የበግና ፍየል ጸጋዎችን ይዘን ለተረጅነት እጃችንን ልንዘረጋ አይገባም ብለዋል።

ያሉትን ጸጋዎች ማኅበረሰቡ እንዲጠቀምባቸው ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እና ያሉትን ክፍተቶች በመለየት መፍትሔ ማስቀመጥ የባለሙያዎች እና የመሪዎች ድርሻ መኾኑን ተናግረዋል። ያሉንን ጸጋዎች በአግባቡ ከተጠቀምን ዋግኽምራን ከተረጅነት ማላቀቅ እንችላለን ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ለዚህም የባለሙያዎቹ ድርሻ የላቀ ነው ብለዋል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንሰሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሲሳይ አያሌው በእንሰሳት ዘርፍ፣ በንብ ምርት፣በዓሳ እና በዶሮ ሃብት በኩል የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ሥራዎች አጥጋቢ አለመኾናቸውን ነው የተናገሩት።

የአተገባበር ችግሮችን በመቅረፍ በዘመናዊ አሠራር መተካት ጸጋዎችን አሟጦ ለመጠቀም ያግዛል ብለዋል። ጸጋዎችን ለመጠቀም ዓላማ ያደረገው እና ለሦስት ቀናት የሚቆየው የውይይት መድረክ የአሠራር እና የአተገባበር አቅማችን ያሳድግልናል ነው ያሉት።

በውይይቱ የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ባለሙያዎች፣ በዘርፉ የሚሠሩ አጋዥ ድርጅቶች፣ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች እና መሪዎች ተሳታፊ ናቸው።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለፀረ ሙስና ትግል ሁሉም ሊያግዝ እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ አሳሰቡ።
Next articleየተሻሻለው የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ፀደቀ።