
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ብልሹ አሠራርን እና ሙስናን ለመከላከል ከሚመለከታቸው ተቋማት እና የሲቪክ ማኅበራት ጋር በጥምረት ለመሥራት ሥምምነት ተፈራርሟል። በሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴን(ዶ.ር) ጨምሮ የክልል ቢሮ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ተቋማት እና የሙያ ማኅበራት ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል አንዱ የሕዝብ ሀብት እና ንብረት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ሥነ ምግባርን በተከተለ መልኩ ሙስናን የመከላከል ሥራን መሥራት መኾኑን አንስተዋል። ተጠያቂነትን አሠራር እንዲሰፍን ለተቋማት ግብዓት ማቅረብንም ጨምረዋል። ለምክር ቤቶች የጠራ መረጃ በማቅረብ እንዲታገሉበት እና የሕዝብ ውክልናቸውንም እንዲወጡ እያደረገ መምጣቱንም አክለዋል።
የጥምረቱ መመሥረት ምክንያትም ተቋማት ከተናጠል ከሚሠሩት በተጨማሪ ኀላፊነታቸውን በጋራ በመሥራት የሙስናን ትግል ለማጠናከር እንደኾነም ነው አፈ ጉባኤዋ የገለጹት። ኮሚሽኑ ጥምረቱን ለማቋቋም የሕግ መሠረት እንዳለውም ጠቅሰዋል። በሥነ ምግባር ግንባታ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ በመፍጠር በኩል የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራት እና ሌሎቹም ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ሥነ ምግባርን ከመገንባት አኳያ የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ኅብረተሰቡ ከተራ አገልግሎት ጀምሮ ለማንኛውም አገልግሎት ክፍያ እየተጠየቀ መኾኑን ያነሱት ዋና አፈ ጉባኤዋ ችገሩን ለመቀነስ ከጥምረቱ መቋቋም በኋላ በሚቀመጡ አሠራሮች አማካይነት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመገንዘብ ሁሉም የአቅሙን ማበርከት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። በየተቋማቱ ከእቅድ ጀምሮ ትኩረት በመስጠት የመሥራት ጅምር ቢኖርም ውጤቱ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም። ይህንን ችግር ለመፍታት የጥምረቱ መመሥረት ታምኖበታል።
የሥነ ምግባር ግንባታውን በየተቋማቱ በመሥራት በትውልድ ላይ የሚሠራውን ሥራ ለማጠናከር ነው። ተቋማት ይህንን ሥራ ለመሥራት የሚያጋጥመውን ችግር በጋራ እየገመገምን የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ጥረት ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
የጥምረቱ መቋቋም ግብ የፀረ ሙስና ትግሉ በተገቢው ተመርቶ ሕዝብ ተገቢ አገልግሎት እንዲያገኝ ምቹ ኹኔታ ለመፍጠር ነው። ለዚህም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አደራ ብለዋል ዋና አፈ ጉባኤዋ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!