
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ፣ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የወሎ ተሪሸሪ ኬር የሕክምና እና የማስተማሪያ ሆስፒታልን አሁናዊ ኹኔታ ገምግሟል። በግምገማውም ወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምና እና የማስተማሪያ ሆስፒታልን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ለመረከብ ዝግጁ መኾን እንዳለበት አሳሳስቧል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ፣ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺ እመቤት ደምሴ ( ዶ.ር) የወሎ ዩኒቨርስቲ ሕጋዊ ተጠያቂነት ያለው የመንግሥት ተቋም በመኾኑ የወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምና እና የማስተማሪያ ሆስፒታልን ለማቋቋም ድጋፍ ያደጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እምነት የሚጥሉበት ተቋም ነው ብለዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ የተጣለበትን እምነት ለመረከብ ከወዲኹ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚገባው አመላክተዋል። የወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምና እና የማስተማሪያ ሆስፒታል ቦርድ ለሠራው ሥራ ምስጋና ቀርቦለታል። ቦርዱ እና የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ በጋራ በመኾን ለኅብረተሰብ ግልፅ በኾነ መንገድ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ሕዝባዊ አደራውን በተገቢው ኹኔታ ለማስተላለፍ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ሚዲያዎች በተገኙበት ሆስፒታሉን መቼ እና በምን ኹኔታ ለዩኒቨርስቲው እንደሚያስተላልፍ የድርጊት መርሐ ግብር አዘጋጅቶ እስከ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያሳውቅም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ፣ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር እና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ሆስፒታሉን በማስተላለፍ ሂደት መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ምክክር ተደርጓል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!