
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች 24 ሰዓት መቆጣጠር የሚችሉ ዘመናዊ ካሜራዎች እየተተከሉ መኾናቸውን የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንድላማው ገልጸዋል። ባሕር ዳር ደኅንነቷ የተጠበቀ እና በሕገ ወጥ ሥራ የማትረበሽ ከተማ ለማድረግ እየተሠራ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለዚህም ከ468 በላይ ዘመናዊ ካሜራዎች የልየታ ሥራ ተከናውኖ ወደ ሥራ ተገብቷል።
የት ቦታ ምን ዓይነት ካሜራ እንደሚያስፈልግም ተለይቷል ነው ያሉት ከንቲባው። የመጀመሪያ ምዕራፍ በአንድ፣ በሁለት፣ በአምስት እና በ10 ኪሎ ሜትር ርቀቶች የሚኖሩ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር የሚያስችሉ ዘመናዊ የሲሲቲቪ ካሜራዎች ተከላ እየተካሄደ ነውም ብለዋል። የካሜራዎቹ ተከላ ተጠናቅቆ ሥራ ላይ ሲውሉ የባሕር ዳር ከተማን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመከታተል እና በመቆጣጠር ከተማዋን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኝዎቿ ምቹ፣ ኮሽታ የማይሰማባት፣ ውብ፣ ጽዱ፣ ማራኪ እና ዘመናዊ ያደርጋታል።
ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ተከታትሎ በመረጃ፣ በማስረጃ እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ተአማኒ ብሎም ቅቡል ርምጃዎችን ለመውሰድ ያስችላል ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው። ካሜራዎቹ በከተማዋ የሚኖረውን የትራንስፖርት አገልግሎት በመቆጣጠር ረገድም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖራቸዋል ያሉት አቶ ጎሹ በአንድ የመቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ የሚገኝ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ኀላፊ ባሕር ዳር ውስጥ የሚኖረውን እንቅስቃሴ መቶ በመቶ ይቆጣጠረዋል ብለዋል።
የትራፊክ ኹኔታው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ስለሚኾንም የት ቦታ ችግር እንደደረሰ አውቆም ፈጣን ትዕዛዝ ለመስጠትም ያስችላል ነው ያሉት። ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ጥፋት ፈጽሞ የሚሰወር ተሽከርካሪ እንደማይኖርም አቶ ጎሹ ጠቁመዋል። መላው ማኅበረሰብም ለሥራው ተባባሪ እንዲኾን ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!