
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለሃብቶቹ ከርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ጋር በኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ተወያይተዋል። በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
የኤኤስ ሆልዲንግስ ሥራ አስፈጻሚ ሩቲ ሩቢን ከርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በውይይቱ የእስራኤል ባለሃብቶች በአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ላይ በሚሳተፉበት ሁኔታ መምከራቸውን ነው የተናገሩት። ውይይቱ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መኾኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ በተለይም የአማራ ክልል ከእስራኤል ባሃብቶች ጋር በጋራ እንደሚሠራ ነው ያመላከቱት።
በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በማዕድን ልማት እና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ለኢንቨስትመንት ምቹ መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉ ለኢንቨስትመንት በቂ የኾነ የሰው ኃይል መኖሩንም አንስተዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የእስራኤል ባለሃብቶች በአማራ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለ ነዋያቸውን በሚያፈስሱበት ሁኔታ መወያየታቸውን ተናግረዋል። ባለሃብቶቹ ከአሁን ቀደም በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት የነበራቸው እና ኢንቨስት እያደረጉ ያሉ ባለሃብት መኖራቸውንም አንስተዋል።
በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ በሚያቀርቡበት ሁኔታ መምከራቸውን ነው የተናገሩት። በቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍም ኢንቨስት በሚያደርጉባቸው ሁኔታዎች መወያያታቸውን ገልጸዋል። የማዕድን ልማት ላይም መወያየታቸውን ነው የተናገሩት። ባለሃብቶቹ በተለያዩ ሀገራት በኢንቨስትመንት ዘርፉ እየተሳተፉ የሚገኙ እና ሰፊ አቅም ያላቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በክልሉ የሥራ እድል በመፍጠር፣ ምርትን ወደ ውጭ በማወጣት፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በመጨመር እና ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ በመተካት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ባለሃብቶቹ ከክልሉ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በመኾን ወደ ዝርዝር ተግባር እንደሚገቡም አመላክተዋል። ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርግ ቡድን ለማደራጀት መስማማታቸውን ነው የተናገሩት።
በአማራ ክልል ከጸጥታ ጥበቃ ሥራው ጎን ለጎን ጥሩ የኢንቨስትመንት ፍሰት መኖሩንም ገልጸዋል። በክልሉ ለኢንቨስትመንት የተመቼ አቅም መኖሩንም ተናግረዋል። የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እና ወደ ሥራ የሚገቡ ኢንዱስትሪዎች ክልሉ በጥሩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ መኾኑን የሚያመላክቱ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት የሚመጡ ባለሃብቶችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እያደረጉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ባለሃብቶችን የሚስብ እና ጉዳይ የሚያስፈጽም ቢሮ አዲስ አበበ ላይ መክፈታቸውንም አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከባለሃብቶች ጋር በመገናኘት ወደ አማራ ክልል የሚመጡበትን ሁኔታ እያመቻቹ መኾናቸውን ገልጸዋል። ባለሃብቶች የሚያነሱትን ጥያቄ እየፈታን የክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር እንሠራለን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!