ከ240 ሺህ በላይ ወገኖች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

21

በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከ240 ሺህ በላይ የሚኾኑ ወገኖች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አሰታውቋል። በክረምት ወቅት በነበረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ምክንያት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደጋማ አካባቢዎች ላይ ጉዳት ተከስቷል።

ድሃና ፣ጋዝጊብላ እና ጻግብጂ ወረዳዎች ደግሞ ጉዳት የደረባቸው ናቸው። በበረዶ እና በጎርፍ ምክንያት ሰብላቸው የተጎዱባቸውን ወገኖች ለመደገፍ ያለመ የውይይት መድረክ በሰቆጣ ከተማ ከባለድርሻ አካለት ጋር ምክክር ተደርጓል። በምክክሩ የደረሰውን ጉዳት የሚያሰይ የዳሰሳ ጥናት መደረጉም ተነስቷል።
በጋዝጊብላ ወረዳ የዳሰሳ ጥናት ያደረጉት የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተወካይ ኃይለሚካኤል አያል በክረምት ወቅት በነበረው ኃይል የቀላቀለ ዝናብ ምክንያት የመሬት መንሸራተት፣ ጎርፍ እና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ መከሰቱን ተናግረዋል።

በተፈጠረው ችግርም ከ49 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች በወረዳው ለአደጋ ተጋላጭ መኾናቸውን በጥናቱ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። ከ271 በላይ የአርሶ አደር ቤቶች በመሬት መንሸራተት እና በጎርፍ አደጋ እንደተደረመሰ የገለጹት ደግሞ በድሃና ወረዳ ጥናት ያደረጉት የአመልድ ኢትዮጵያ ተወካይ በላይነህ አናውጤ ናቸው።

በተፈጠረው ችግር ከ107 ሺህ በላይ የሚኾኑ የድሃና ወረዳ ነዋሪዎች ለማኅበራዊ ቀውስ ተጋላጭ ናቸው ብለዋል። የጥናቱ ውጤት ለአጋዥ ድርጅቶች በማቅረብ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች በዘላቂነት የሚደገፉበትን እድል ለማመቻቸት እንደሚሠሩ አጥኝዎቹ ተናግረዋል። መንግሥትም ለአጋዥ ድርጅቶች ምቹ ኹኔታን በመፍጠር በኩል እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምህረት መላኩ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደጋማ አካባቢዎች ላይ በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ከ242 ሺህ 800 የሚኾኑ ወገኖች ተጎድተዋል ነው ያሉት። ከ700 በላይ የሚኾኑ የቤት እንሰሳት በጎርፍ ሲወሰዱ ከ49 ሽህ ሄክታር በላይ ሰብል በጎርፍ ጉዳት ደርሶበታል ነው ያሉት።

እስካሁን በክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በኩል የተላከ 400 ኩንታል እህል ለድሃና እና ጋዝጊብላ ወረዳዎች መከፋፈሉን ገልጸዋል። በዋግ ልማት ማኅበር በኩል ደግሞ ግምቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚኾን 220 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች በማከፋፈል በበጋ መስኖ እንዲጠቀሙ ለማድረግ መደገፋቸውን ነው የተናገሩት።

የሚደረጉ ድጋፎች ጊዜዊ እንጂ ዘላቂ አይደሉም ያሉት ኃላፊው አጋዥ ድርጅቶች እና መንግሥት ችግሩ ተስፋፍቶ አሳሳቢ ደረጃ ከመድረሱ በፊት እርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በውይይቱ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች፣ ከ12 አጋዥ ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች እና አጥኝዎች ተሳትፈዋል።
የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መደገፍ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጧዋል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

Previous articleየወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻ ማሽን በድጋፍ አገኘ።
Next articleየእስራኤል ባለሃብቶች በአማራ ክልል ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናገሩ።