የወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻ ማሽን በድጋፍ አገኘ።

35

ወልድያ: ታኅሣሥ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጤና ሚኒስቴር እና በክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሸቲቭ የጋራ ትብብር በግሎባል ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ ማሽኑ የተገዛ መኾኑን የሆስፒታሉ ሥራ አሥኪያጅ ፍስሀ የኋላው ገልጸዋል። ሆስፒታሉ እስካሁን ኦክስጅን የሚያመጣው ከደሴ በመኾኑ የመጓጓዣን ጨምሮ በዓመት እስከ 5 ሚሊዮን ብር ያወጣ ነበር ብለዋል።

ማምረቻው በቀን 200 ሲሊንደር የመሙላት አቅም አለው ያሉት ሥራ አሥኪያጁ የሆስፒታሉ የዕለት ግልጋሎት 25 ሲሊንደር መኾኑን ገልጸዋል። ቀሪው ለሰሜን ወሎ ዞን እና ለዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና ተቋማት አገልግሎት የሚውል መኾኑን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ፈለቁ መኮነን በዞኑ አምስት ሆስፒታሎች እና 69 ጤና ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ሁሉም ሆስፒታሎች ኦክስጅን ይጠቀማሉ ሦስት ጤና ጣቢያዎች ቀዶ ጥገና ጀምረዋል፤ ስድስት ጤና ጣቢያዎች ደግሞ ቀዶ ጥገና ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስረድተዋል። በሁሉም ጤና ጣቢያዎች ደግሞ ድንገተኛ ክፍል ላይ ኦክስጅን እንዲኖር እየተሠራ ነውም ብለዋል። የኦክስጅን ማምረቻ ማሽኑ በሆስፒታሉ መተከል ለእነዚህ ሁሉ ተቋማት የኦክስጅን አቅርቦት በቅርብ ለማድረስ ስለሚያስችል የጊዜ፣ የገንዘብ እና የጉልበት ወጭን ይቀንሳል ነው ያሉት።

ኦክስጅን ሲያልቅ እና ከደሴ እስከሚመጣ የሆስፒታሉ ታካሚዎች ይንገላቱ ነበር ያሉት የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ማምረቻ ማሽኑ መምጣቱ የሕዝቡን ችግር ያቃልላል ብለዋል።

ሆስፒታሉ አቅሙን እና ደረጃውን ለማሳደግ የሚያደረገውን ጥረትም ከተማ አሥተዳደሩ እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል የተሳታፊ እና የአጀንዳ ልየታ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
Next articleከ240 ሺህ በላይ ወገኖች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።