
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለዘመናዊ ከተማ ዘመናዊ ትራንስፖርት ያስፈልጋል ብለዋል። በመኾኑም በባሕር ዳር ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ባጃጅ ሕጋዊ ኾኖ ሕዝብን እንዲያገለግል በመለያ ቁጥር (ባር ኮድ) መቆጣጠር አስፈላጊ ኾኗል ብለዋል።
በከተማዋ 18 ያህል የባጃጅ ማኅበራት አሉ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ ከ10 ሺህ በላይ ባጃጆችም ይገኛሉ ነው ያሉት። እነዚህ ባጃጆች በሕጋዊ መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ አስፈላጊ እንደኾነም አስረድተዋል። በሌላ በኩል ባጃጆችን ተጠቅሞ ሕገ ወጥ ተግባር እንዳይከናወንም መለያው ተግባር ላይ ውሏል ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ከታኅሣሥ 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ በማኅበር ሳይደራጁ እና መለያ (ባር ኮድ) ያላደረጉ ባጃጆች አገልግሎት አይሰጡም ነው ያሉት። ማንኛውም ዘመናዊ ስልክ ያላቸው ተገልጋዮች የሚሳፈሩበት ባጃጅ የማን እንደኾነ እስከ ማኅበሩ ስም ድረስ እንዲያውቁ ያግዛልም ብለዋል።
ኅብረተሰቡም መለያ (ባር ኮድ) በኋላው እና በጎኑ ያለጠፈን ባጃጅ ሲመለከት ለጸጥታ አስከባሪዎች በመጠቆም በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል እንዲተባበርም ጠይቀዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስንታየሁ ዘለቀ የትራንስፖርት ዘርፉን አዘምኖ እና ሕገ ወጥ ባጃጆችን ከሕጋዊው ለመለየት የሚያስችል ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ መዋሉ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል።
ሁሉም ባጃጆች የመለያ (ባር ኮድ) ለጥፈው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አለባቸው ብለዋለሰ አቶ ስንታየሁ። የባጃጅ ማኅበራትም ዝርዝር መረጃዎችን በሥራቸው ለሚያሥተዳድሯቸው ባጃጅ አሽከርካሪዎች እና ለትራንስፖርት ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
አቶ ስንታየሁ ተገልጋዩ ማኅበረሰብም የሚጠቀመውን ባጃጅ ሕጋዊነት በመለያው አይቶ ከመጠቀም ባለፈ ባር ኮድ የሌለውን ባጃጅ ለጸጥታ አስከባሪዎች እንዲጠቁምም ነው ያሳሰቡት። በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ደኅንነት እና ትራፊክ ዋና ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር አብርሃም ልየው ለባጃጆች መለያ (ባር ኮድ) መሰጠቱ ሕጋዊውን ባጃጅ ከሕገ ወጡ በቀላሉ በመለየት ወንጀልን በዘመናዊ መንገድ በመቆጣጠር ብሎም ለሕግ ለማቅረብ ያስችላል።
“ባር ኮዱ የባጃጁን አድራሻ ያሳያል፤ የየትኛው ማኅበር አባል እንደኾነም መረጃ ይሰጣል፤ ወደ ባሕር ዳር ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡትን ባጃጆችንም ለመቆጣጠር ይጠቅማል፤ በመኾኑም ወንጀል በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው” ነው ያሉት። ለአሚኮ ሃሳባቸውን የሰጡ የባጃጅ አሽከርካሪዎችም “የመለያ ኮዱ ሕዝቡ እንዲያምነን ስለሚያደርግ ገቢያችን እንዲጨምር ያግዘናል” ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!