
ደብረ ማርቆስ: ታኅሳስ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ሠራተኞች የግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበርን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ በማጠናከር የአባላቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን በምሥራቅ ጎጃም ዞን የጎዛምን ወረዳ ገልጿል። የጎዛምን ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበር በቅርቡ ከተመሠረቱ የሸማች ማኅበራት መካከል አንዱ ነው።
ማኅበሩ አሁን ላይ 541 የመንግሥት ሠራተኞችን በአባልነት የያዘ ሲኾን በወረዳው በተመቻቸለት 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ወደ ሥራ ገብቷል። ማኅበሩ በተራዘመ የጊዜ ክፍያ በሚያቀርበው የጤፍ እና ስኳር ምርት የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም እንዳገዛቸው አባል የመንግሥት ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡
ከኅብረት ሥራ ማኅበሩ በቀጣይ የበለጠ ተጠቃሚ ለመኾን የማኅበሩ ገቢ እንዲጨምር የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል። የጎዛምን ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበር ሠብሣቢ በልስቲ ስሜነህ የወረዳው አሥተዳደር ባመቻቸው ተዘዋዋሪ ብድር የአባላትን ፍላጎት እና የመክፈል አቅም ታሳቢ በማድረግ በተራዘመ ክፍያ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት፡፡
አሁን ላይ ማኅበሩ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እየሠራ መኾኑን የተናገሩት ሠብሣቢው በቀጣይ ማኅበሩን በማስፋት እና ገቢውን በማሳደግ ራሱን ለማሰቻል እንደሚሠራ ተናግረዋል። የጎዛምን ወረዳ አሥተዳዳሪ ሙሉሰው ቀሬ የግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበሩን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ የበለጠ ለማሳደግ እና ለማጠናከር አሥተዳደር ምክር ቤቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
ማኅበሩ ከተመቻቸለት ተዘዋዋሪ ብድር በተጨማሪ ወረዳው የ1ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማጽደቁንም ተናግረዋል። የጎዛምን ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ሸማች ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበር አሁን ላይ 541 አባላትን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ከወራዳው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!