
ገንዳ ውኃ: ታኅሣሥ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ እቃ ጭኖ የነበረ አንድ የደረቅ ጭነት አይሱዙ መኪና በጥቆማ በጸጥታ ኀይሎች መያዙን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ኢንስፔክተር ኃይሌ ብርሃኑ እንደገለጹት ማኅበረሰቡ ባደረገው ትብብር እና ጥቆማ መሠረት የኮንትሮባንድ ዕቃ የጫነ ተሽከርካሪ ተይዟል።
ተሽከርካሪው ልዩ ቦታው በከተማው ቀበሌ 03 ቀጣና 05 ተደብቆ የቆመ እና የሰሌዳ ቁጥር የሌለው መኾኑን አስረድተዋል አሽከርካሪው እንዳልተያዘ እና በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል ክትትል እየተደረገ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ከተያዘው እቃ መካከል የሳሙና ምርት፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እና የፒጃማ አልባሳት ይገኙበታል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ መያዙን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!