
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በባጃጆች አማካኝነት የሚፈጸምን ወንጀል ለመከላከል የሚያስችል የመለያ “ባር ኮድ” መስጠት መጀመሩን ከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል። የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማዋ ከ10 ሺህ በላይ ባጃጆች ስለሚገኙ በዘመናዊ መንገድ መቆጣጠር አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል ብለዋል።
በመኾኑም ዛሬ መሰጠት የተጀመረው የመለያ “ባር ኮዱ” ሕጋዊ ባጃጆችን ከሕገ ወጦች በቀላሉ በመለየት ኅብረተሰቡን ከመጭበርበር ይታደጋል ነው ያሉት። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በከተማዋ ያለውን የባጃጅ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመንም የመለያ ባር ኮዱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ተሳፋሪው የባጃጁን መለያ “ባር ኮድ” በስማርት ስልክ ስካን በማድረግ የባጃጁን ማኅበር እና የባለቤቱን ስልክ ቁጥር ማወቅ ያስችለዋል ነው ያሉት።
“ከታኅሣሥ 07/2017 ዓ.ም ጀምሮም ኅብረተሰቡ መለያ ባር ኮድ በሌለው ባጃጅ መሳፈር የለበትም” ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!