
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የተጀመረው በሕትመት ሚዲያው በበኩር ጋዜጣ ነበር። ታኅሳስ 7 1987 ዓ.ም በአማራ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ሥር በአንድ የሥራ ሂደት ሥር መታተም የጀመረችው በኩር ጋዜጣ ዝግጅት ለአሁኑ የአሚኮ መሠረት ናት። እንደ ስሟ ሁሉ የአሚኮ በኩር ናት።
ከሠላሣ ዓመታት በፊት በጋዜጣ፣ ከአሥር በማይበልጡ ጋዜጠኞች ቴክኖሎጂ በሌለበት እና በማይመች የሥራ ኹኔታ በኩር ጋዜጣ እየተዘጋጀት እና እየታተመች መሠራጨት ጀመረች። አሁን 30ኛ ዓመቷን ይዛለች። የአሚኮ መሪዎች እና ሠራተኞችም የበኩርን የምስረታ ቀን በውይይት እና በተለያዩ ዝግጅቶች ዘክረዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ንግግር ያደረጉት የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ የበኩር መሥራቾች እና ጋዜጠኞች ሥራውን በችግር እና ፈተና ውስጥ ኾነው መጀመራቸውን አስታውሰዋል። አሁን ያለነው የአሚኮ ሠራተኞችም ኮርፖሬሽኑን ለቀጣይ ሠላሣ ዓመታት የሚደርስበትን ደረጃ አስበን ማቀድ እና በኀላፊነት መሥራት አለብን ነው ያሉት።
ምቹ ኹኔታዎች ሁልጊዜ እንደማይገኙ ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው ሥራችንን በምቹ ኹኔታ ብቻ ሳይኾን ችግርን እየተጋፈጥን በመሥራት ለተሻለ የተቋም ግንባታ መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል። የአሁኑ ፈተና የቁሳቁስ ሳይኾን ሰው ልብ ውስጥ የሚገባ ዘገባ የመሥራት ጉዳይ ነው መኾኑንም አንስተዋል። ለሰላም እና ለልማት በትጋት በመሥራት ኅብረተሰብን ማገልገል ይገባል ነው ያሉት።
በአማርኛ ብቻ ትታተም የነበረች የአሚኮ በኩር ጋዜጣ ከዓመታት በኋላ ለሌሎች ቋንቋዎች መሠረት ኾናለች። አሁን በኦሮምኛ፣ በአዊኛ፣ በኽምጣኛ ቋንቋዎች የሚታተሙ ጋዜጦች ለሕዝብ ይደርሳሉ። ከሠላሣ ዓመታት በፊት በበኩር ቀዳሚነትን የጀመረው አሚኮ ዛሬ ላይ ጉዙፍ የሚዲያ ተቋም ኾኗል። ልሳነ ብዙ እና ኅብረ ብሔራዊ የኾነ ለኅብረተሰብ ለውጥ እየተጋ የሚገኝ የሚዲያ ተቋምም ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!