ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።

36

እንጅባራ: ታኅሣሥ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማ አሥተዳደሩ “ሴት የሰላም እናት”በሚል መሪ ሃሳብ ሴቶች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የፀጥታ ችግር በሴቶች ላይ ተደራራቢ ችግሮችን ማስከተሉን ተናግረዋል።

ሟች እና ገዳይ ያልተለየበት የእርስ በእርስ ግጭት ክልሉን የከፋ ቀውስ ውስጥ ከትቶታል ያሉት ተሳታፊዎቹ የታጠቁ ኀይሎች ለሰላማዊ ንግግር ቅድሚያ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

ቀውሱን ያባባሱ የአልግሎት አሰጣጥ፣ የዋጋ ንረት እና የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባም አንስተዋል።

አሁን ላይ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነቱ እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁ መኾናቸውንም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ በከተማ አሥተዳደሩ አሁን ለተገኘው አንፃራዊ ሰላም የሴቶች አበርክቶ የጎላ እንደነበር ተናግረዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ሴቶችን ያላሳተፈ የልማት እና የሰላም አጀንዳ ዘላቂ እንደማይኾን ተናግረዋል።

የዋጋ ንረትን ለማርገብ በንግድ ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥነቶችን መከላከል እና የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በገንዘብ የማጠናከር እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደኾነም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዘላቂ ሰላም ለማፅናት የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ዋና አሥተዳዳሪው አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወታደራዊ ሥልጠና ያጠናቀቁ ሚሊሻዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መዘጋጀታቸውን ተናገሩ።
Next articleርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ከእስራኤል ባለሃብቶች ጋር እየተወያዩ ነው።