
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተሟላ መልኩ ወደ ሥራ ለማስገባት የተቋቋመ ስትሪንግ ኮሚቴ በተግባራት አፈጻፀም ላይ ውይይት አካሄዷል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኅላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ውይይቱን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪዎች የግብርና ዕሴት ሰንሰለትን የማሳደግ እምቅ አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል። በውይይቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ዝርዝር አፈጻጸም፣ ያሉበት ደረጃ እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በዝርዝር ታይቶ የቀጣይ አቅጣጫም ስለመቀመጡ ጠቁመዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ለመግባት በተጨባጭ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተለይተዋል፤ ችግሮቹ በፍጥነት እንዲፈቱም መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት ዶክተር አሕመዲን።
ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃዎችና የኃይል አቅርቦት እንዲሟላላቸው መሥራት ለሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
ከምንም በላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማነት ሰላምን ስለሚሻ የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት አለብን ሲሉ አሳስበዋል። የባለድርሻ አካላትን ትብብርና ቅንጅት ታሳቢ ያደረገ የተግባር እንቅስቃሴ በማድረግ ፓርኮቹ ለሀገር ዕድገት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲያሳኩ እየሠራን ነው ብለዋል ኀላፊው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!