
ጎንደር: ታኅሣሥ 6/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የሌማት ትሩፋቶችን እና የግብርና ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በከተማው የእንስሳት እርባታ ልማት እያደገ እንደሚገኝ አንስተዋል። ሚኒስትሩ የመኖ አቅርቦት እና የደሮ እርባታ የእንቁላል ምርት ላይ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን በመስክ ምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ነው የገለጹት። የወንዝ ዳርቻን ተከትሎ የሚለማው የፍራፍሬ ልማት ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ምርቱን ወደ ማኅበረሰቡ በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን የሚያረጋጋ መኾኑን ተናግረዋል። በዘርፉ የተሠማሩ ግለሰቦች በክልሉ የጸጥታ ችግር ቢኖርም ችግሩን ተቋቁመው በመሥራት እና ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በቅንጅት ተግባራትን በመከወን ውጤታማ ኾነዋል ብለዋል። በትንሽ የተጀመሩ ልማቶች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በማሳደግ ውጤታማ መኾን እንደቻሉ ተመልክተናል ነው ያሉት። በከተማ አሥተዳደሩ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ማረጋገጣቸውንም አብራርተዋል።
ለአልሚዎች የቦታ አቅርቦት፣ ለመኖ ማቀናበሪያ ግንባታ የብድር አገልግሎት እና ግንባታ ለማከናወን ከመንግሥት መዋቅር ጋር በማቀራረብ ያሉባቸው ችግሮች እንዲቀረፉ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው 60 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ በአንድ ሸድ ውስጥ የልማት ተግባራትን ለማከናወን እንዲችሉ መሠራቱን አስገንዝበዋል። 12 የደሮ ሸዶችን በመገንባት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ መሠራቱንም ነው የገለጹት።
በቦታ ጉዳይ የሚገጥሙ ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ እና በተበታተነ ቦታ ከማልማት ይልቅ በአንድ ማዕከል ለማሠማራት ሸድ መገንባቱን ገልጸዋል። በቀጣይ ለእንስሳት እርባታ እና ለወተት አስተዋጽኦ የሚያገለግሉ ክላስተሮችን ለመገንባት መታቀዱን አንስተዋል።
በአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ልማት ለተሠማሩ አልሚዎች የግብዓት አቅርቦትን ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል።
አልሚዎች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው። በዘርፉ የተሠማሩ አልሚዎች በበኩላቸው ከዘርፉ ተጠቃሚ መኾናቸውን አንስተዋል። ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!