✍️ የጽናት እና የነጻነት ተምሳሌት!

119

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 6/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጽናት እና የነጻነት ቁንጮ በመኾን መላው ዓለም ከሚስማማባቸው አንዱ ናቸው ኔልሰን ማንዴላ። ማንዴላ አይበገሬ የሚለው ስያሜያቸውም ጥያቄ አይነሳበትም።
ማንዴላ በዓለማችን ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ተደማጭነት እንዲሁም ተጽዕኖ መፍጠር ከቻሉ መሪዎች መካከል አንዱ እንደኾኑ በታሪክ መዝገብ ላይም ሰፍረዋል።

ገና በወጣትነታቸው የነጭን ጭቆና ተጸይፈው ትግል አደረጉ። በትግላቸው እስር ቤት ወደቁ። በእስር ቤትም 27 ዓመታትን አሳለፉ። ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ በእስር ያሳለፉት ኔልሰን ማንዴላ ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ ባላቀቀው ሕገ መንግሥት ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት በዚህ ሳምንት ነበር።

የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት እና የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ የጥቂት ነጮች አገዛዝ (አፓርታይድ) ማብቂያውን አግኝቶ ደቡብ አፍሪካን ወደ ዴሞክራሲ የሚያሸጋግራትን አዲስ ሕገ መንግሥት የፈረሙት ልክ በያዝነው ሳምንት እንደ አውሮጳውያኖቹ ዘመን ታኅሣሥ 10/1996 ነበር። ማንዴላ ለደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይኾን ለመላው ዓለምም የነፃነት ታጋይ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ የፖለቲካ መሪ እና የእርቅ ተምሳሌት መገለጫም ናቸው። ኔልሰን ማንዴላ ለሦስት አስርት ዓመታት ገደማ በዘለቀው የእስር ሕይወት ሳይበገሩ የደቡብ አፍሪካ መሪ ኾነው በርካታ ማሻሻያዎችን ጭምር አምጥተዋል።
የአፓርታይድ ሥርዓት እንዲወገድ ድርድር መደረጉንም ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ለመኾንም በቁ። ከአንድ የፕሬዚዳንትነት ዘመን በኋላም ሥልጣን ለቀቁ። በ95 ዓመታቸውም በአውሮጳውያኑ የዘመን አቆጣጠር ታኅሣሥ 2003 አረፉ።

✍️ የመጀመሪያው የትራፊክ መብራት!
በዓለም ላይ የመጀመሪያው የትራፊክ መብራት በእንግሊዝ የተተከለው እንደ አውሮጳውያኑ ዘመን በያዝነው ሳምንት ታኅሣሥ 9/1868 ነበር። በዓለም ላይ የመጀመሪያው የትራፊክ መብራት የቆመው በእንግሊዝ ለንደን ዌስትሚኒስትር ድልድይ ላይ ነው። ይሁን እንጂ መብራቱ እንዲበራ የኀይል ምንጭ የነበረው ጋዝ አፈትልኮ ፍንዳታ በመፍጠሩ ብዙም ሳይቆይ እንደታሰበው ስኬታማ ሳይኾን ቀርቶ ከቆመበት ሊነሳ ችሏል። ይህ ጅምር ሃሳብ ግን አድጎ እንደ አውሮጳውያኑ ዘመን በ1926 እውን ለኾነው የትራፊክ መብራት መሠረት እንደጣለ ይነገርለታል።

✍️ የኬንያ ነጻነት!
ኬንያ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነፃ ሀገር መኾኗን ያወጀችው እንደ አውሮጳውያኑ ዘመን በያዝነው ሳምንት ታኅሣሥ 12/1963 ነበር። ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኬንያ ለዓመታት በቅኝ ግዛት ስታስተዳድራት ከነበረችው ብሪታንያ ነፃ የወጣችው በያዝነው ሳምንት ነው። ለ43 ዓመታት የዘለቀው የብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ በኬንያውያን ጠንካራ ሀገራዊ ትግል ሊያከትም ችሏል። ብሪታንያ ይህን የኬኒያውያን ነጻነት ለማስቀረት 55 ሚሊዮን ፓውንድ ፈሰስ ማድረጓም ይነገርላታል።

ብሪታንያ የኬኒያውያን ነጻ የመኾን ፍላጎትን ተከትሎ ለጊዜው የተለያዩ ማሻሻያዎችን እንድታደርግ በማስገደድ ኬንያውያን የሚሳተፉበት ሕግ አውጭ ምክር ቤት በመመስረት እንግሊዛዊያን ብቻ ይዘዋቸው በነበሩ የንግድ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ እስከማድረግ አድርሷቸውም ነበር። የኋላ ኋላ የማኡ ማኡ እንቅስቃሴን ጀሞ ኬንያታ መርተው እንደ አውሮጳውያኑ ዘመን በ1963 የኬንያ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር በመኾን የሽግግር ጊዜ መሪ እንዲኾኑ ተመረጡ። በመጨረሻም ኬንያ በታኅሣሥ ወር በያዝነው ሳምንት ከብሪታኒያ ነፃ ወጥታለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላም ለማጽናት የመንግሥት እና የግል ታጣቂዎች በንቃት እንዲጠብቁ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደሩ አሣሠበ።
Next article“የሌማት ትሩፋት እና የግብርና ሥራዎች ውጤት እያስመዘገቡ ነው” መላኩ አለበል