ሰላም ለማጽናት የመንግሥት እና የግል ታጣቂዎች በንቃት እንዲጠብቁ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደሩ አሣሠበ።

45

ባሕር ዳር: 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም “በሚል መሪ ሃሳብ የመንግሥት እና የግል ታጣቂዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው። ከስድስቱም ክፍለ ከተሞች የተወከሉ ታጣቂዎች “ሰላም የሁሉም መሠረት ነው። አካባቢያችንን ተደራጅተን በመጠበቅ ለሰላም የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን!” የሚሉ መፈክሮችን አንግበው ነው እየተወያዩ ያሉት።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ሰላም ቅድመ ኹኔታ የማያስፈልገው ለፍጥረታት ሁሉ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል። ሰላም በደፈረሰ ጊዜ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፤ በመኾኑም አንዱ ለሁሉም ሁሉም ለአንዱ ሰላም መኾን ዘብ መቆም ይገባዋል ነው ያሉት። በክልሉ ተከስቶ የቆየውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋት ከፍተኛ ሥራዎች መከናወናቸውን ምክትል ከንቲባው አስታውሰዋል።

ሰላም ደፍርሶ፣ ተኩስ ነግሶ፣ ሰው ወጥቶ ለመግባት ሲቸገር የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የጸጥታ ኃይላት ጋር በመቀናጀት የመንግሥትን ሥርዓት ከመፍረስ አደጋ ታድጓዋል ብለዋል። እንደ ከተማ ሰላም በጠፋበት ወቅት በከተማ አሥተዳደሩ ከቀበሌ እስከ ክፍለ ከተሞች ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸው ለተገኘው ሰላም ድርሻ ነበረው ነው ያሉት። ሕዝባዊ ውይይቶቹ ከተማዋን በማረጋጋት በኩልም ጥሩ ግብዓት ተገኝቶበታልም ብለዋል።

ከአንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ማሸጋገር ተችሏል ያሉት አቶ አስሜ ተቀዛቅዞ እና ተዳክሞ የቆየውን ምጣኔ ሐብት፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴ፣ ኢንዱስትሪ፣ ሁሉን አቀፍ የግብዓት አቅርቦት እና የምርት ዝውውር እንዲኹም ያሻቀበውን ሥራ አጥነት ለመቀነስ ተግቶ መሥራት ይጠይቃል። በውይይቱ ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የከተማ አሥተደደሩ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተገኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቡና ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ930 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ጠቅላላ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ።
Next article✍️ የጽናት እና የነጻነት ተምሳሌት!