
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቡና ባንክ አክሲዮን ማኅበር የባለአክሲዮኖች 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ አካሂዷል። በጉባኤው የ2015/2016 በጀት ዓመት ባንኩ ያከናወናቸው ጠቅላላ ተግባራት ቀርበዋል።
አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 15 ዓመታትን ያስቆጠረው ቡና ባንክ አዳዲስ ቴክኖሎጅን በመጠቀም ለደንበኞች አስተማማኝ፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው ዘመናዊ የፋይናንስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የቡና ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር ዓለማየሁ ሰዋገኝ ተናግረዋል። ባለፈው በጀት ዓመት እንደ ሀገር በተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች በተከሰቱ ግጭቶች የባንኪንግ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ተግዳሮት ተጋርጦበት እንደነበር የቦርዱ ሊቀመንበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጅ ፈተናዎች በመቋቋም በተጠናቀቀው 2015/2016 በጀት ዓመት ከግብር በፊት ከ930 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን አንባሳደር ዓለማየሁ ተናግረዋል። ይህ ትርፍ ከ2014/2015 የበጀት ዓመት የትርፍ መጠን ጋር ሲነጻጸር የ429 ሚሊዮን ብር ቅናሻ አሳይቷል ነው ያሉት።
ባንኩ የቅርንጫፍ አድማሱን በማስፋት ለደንበኞች ያለውን ተደራሽነት ብሎም የሒሳብ አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር ለማሳደግ በርካታ ተግባራት መሥራቱን የቦርዱ ሊቀመንበር ተናግረዋል።
የባንኩ ቅርንጫፎች 474 እንደደረሱ ጠቁመዋል። የተቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም ከ4 ሚሊዮን በላይ መድረሳቸውን አሳውቀዋል።
አጠቃላይ የባንኩ የሃብት መጠን 54 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲኾን ይህም አሃዝ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል ነው ያሉት።
የባንኩ አጠቃላይ የካርድ ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ413 ነጥብ 8 ሺህ በላይ እንደደረሱም ገልጸዋል። በሞባይል እና ኢንተርኔት ባንኪንግ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መደረጉም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!