
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ በዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ በሕጋዊ ካዳስተር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል። መሬት ለአንድ አገር የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ድርሻ ያለው ውስን የተፈጥሮ ሃብት ነው። ይህንን ሃብት ለማሥተዳደር የተደራጀ እና አስተማማኝ መረጃ አስፈላጊ ነው።
እያንዳንዱን ቁራሽ መሬት ለይቶ በማን እንደተያዘ፣ እንዴት እንደተያዘ እና መገኛውን እና ስፋቱን አረጋግጦ በመመዝገብ መረጃውን የማደራጀት ሥራ እየሠራ መቆየቱን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ አስታውቋል።
ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል በባሕር ዳር ከተማ በዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ በቀጠና 08 የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ(ሕጋዊ ካዳስተር ) ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
በግንዛቤ ማስጨበጫው የይዞታ ማረጋገጥ ምንነት እና ዘዴዎች፣ የመሬት ይዞታ የምዝገባ ዓላማዎች፣ የመሬት ይዞታ መብት ማረጋገጫ መርኾች በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች በከተማ አሥተዳደሩ የመሬት መምሪያ ባለሙያ ተክሌ ብርሃኔ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ከተሳታፊዎች ይዞታን ለማረጋገጥ ምን ምን ሰነዶችን ማሟላት አለብን? ካዳስተር ለማኅበረሰቡ ያለው ጠቀሜታ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎች ባለሙያው ባለይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ ለማድረግ ማሟላት ያለባቸው ሰነዶች ይዞታው ባገኙበት አግባብ ይኾናል ነው ያሉት። ለአብነት በምሪት ያገኙ ከኾነ ካርታ፣ የምሪት ደረሰኝ፣ የቦታ ኪራይ ደረሰኝ እና ተያያዥ ሰነዶችን ማሟላት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ካዳስተር ማለት ደግሞ ዘመናዊ የመሬት መረጃ ነው። ይህም ከመሬት እና መሬት ነክ ጋር ተያይዞ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ፈጣን እና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለማሥተዳደር የሚረዳ የመሬት መረጃ ሥርዓት መኾኑን አብራርተዋል። የይዞታ ማረጋገጥ ተግባራትን ለማከናወን ከኅብረተሰቡ የቅሬታ ሰሚ አባላት እና ታዛቢዎች ተመርጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!