
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሀገር በዳኝነት እና በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ መነሻ በማድረግ ክልል አቀፍ የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎቱ ላይ ሁሉ አቀፍ የለውጥ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከያዛቸው አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ውስጥ አንዱ በሆነው የግልግል ዳኝነት ምንነት እና አፈጻጸም ላይ ምሁራንን ጋብዞ ውይይቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በውይይቱ ላይ ዓለምአቀፍ የግልግል ዳኝነት ባለሙያ እና ተመራማሪ ልዩ ታምሩ፣ ስለግልግል ዳኝነት ምንነት እና አጠቃላይ የሀገራትን ተሞክሮ ያቀረቡ ሲሆን፣ የፍትሕ ሚኒስቴር የፍታብሔር ፍትሕ አሥተዳደር ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ንጉሴ ትዕዛዙ የኢትዮጵያን የግልግል ዳኝነት የፖሊሲ እና የሕግ መዕቀፎች፣ እንዲሁም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ የውይይት መነሻ ጽሑፎችን አቅርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
እንደ ሀገር በዘርፉ ላይ ብዙ ያልሠራናቸው ጉዳዮች አሉ ያሉት የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅራቢዎቹ ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከተለያዩ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ባለሙያዎችን፣ የከፍተኛ ትምህርት እና የምርምር ተቋማት ምሁራንን በግልግል ዳኝነት እና አስፈላጊነት እንዲሁም አተገባበር ላይ ማወያየቱ ሀገሪቱ ዘርፉን ለማስፋት ለያዘችው እቅድ ትልቅ ግብዓት ነው ብለዋል።
በቀረቡ የመነሻ ጽሑፎች ላይ ተሳታፊዎችን ያወያዩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለም አንተ አግደው፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኢትዮጵያን የግልግል ዳኝነት ማእከል ለማድርግ ለተያዘው እቅድ ትልቅ አቅም ሊፈጥር የሚችል፣ የግልግል ዳኝነት የስልጠና ማእከል ለማቋቋም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የግልግል ዳኝነት ማእከል ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ብቁ ባለሙያዎችን ከማፍራት እና አስቻይ የሕግ ማእቀፎችን ከማዘጋጀት አንጻር ግን ብዙ መስራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያዘጋጀው ውይይትም የዚህ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።
በቀረቡ የውይይት መነሻ ጽሑፎች ላይ ገንቢ አስተያይታቸውን የሰጡ፣ ኀላፊዎች፣ ምሁራን እና ተመራማሪዎች ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በግልግል ዳኝነት አተገባበር እና ተፈጻሚነት ላይ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት መግለጻቸውን ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!