ዘመናዊ የሕጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝን ለማጠናከር ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ።

44

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለችግር ተጋላጭ ህጻናት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል የተባለውን በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በይፋ ሥራ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ ሥርዓቱ ለችግር ተጋላጭ ህጻናትን መረጃ በዘመናዊ መልኩ ለመያዝ እና ለመቀባበል ስለሚያስችለው ሥርዓት ውይይት ተደርጓል።

በፌዴራል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህጻናት መብት እና ጥበቃ መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ከፍተኛ ባለሙያ ዓለሙ ወልዴ ለችግር የተጋለጠ ህጻን መረጃ የሚያዘው እና የሚጣራው በወረቀት እንደነበር ገልጸዋል።

በዳታ ቤዝ መጀመሩ የህጻናት ሚስጥር የመባከን፣ መረጃው የመጥፋት፣ አድካሚነቱን እና የመረጃ ልውውጡንም እንደሚያቀልለው ተናግረዋል።

በሀገር ደረጃ በስምንት ክልሎች የሙከራ ትግበራ ሲሠራ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ዓለሙ በአማራ ክልልም በስድስት ጣቢያዎች እንዲተገበር ለሶሻል ወርከሮች ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

ዲጂታላይዝድ የኾነው የመረጃ አያያዝ እና ልውውጥ የመረጃውን ሚስጥራዊነት፣ ደኅንነት እና ፍጥነት እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።

የአገልግሎት ዘላቂነትም እንደሚኖረው ነው የገለጹት።

ካለው የሃብት ውስንነት አኳያ በስድስት ጣቢያዎች የተወሰነው የህጻናት ደኅንነት እና ጥበቃ መረጃ አያያዝ ሥርዓቱ እንዲሰፋ እና ሁሉም ህጻናት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ቁሳቁስ፣ የሰው ኃይል ማሟላት እና ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።

በዩኒሴፍ የአማራ ክልል ተወካይ ኀላፊ ዓምባነሽ ነጮ (ዶ.ር) በወረቀት የሚዘጋጀው የህጻናት ጥበቃ መረጃ ውሳኔ ለመስጠት እና ለመሥራት ያለበትን ውስንነት አመላክተዋል።

መረጃውን ለማዘመን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሃሳቡን አመንጭቶ ከክልሉ ቢሮ ጋር ለመሥራት በመቻሉ እና በጋራ ጥረት ለዚህ በመድረሱ አመሥግነዋል።

የተወሳሰበ ችግር ባለበት ክልል ውስጥ ህጻናት እና እናቶች የጥቃት ሰለባዎች ናቸው ያሉት ዶክተር አምባነሽ ዩኒሴፍ ለችግሮች መፍትሄ የመረጃ መሠብሠብ እና ልውውጡን ለማዘመን የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የሕጻናት ጥበቃ መረጃን ዛሬ ጀምረነዋል፤ ይህንኑ ጅምር አሠራር ሁላችንም በመንከባከብ፣ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ሁሉም ለህጻናት ድጋፍ እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።

በአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የባሕር ዳር ከተማ ሶሻል ወርከር ጸጋ የማነ የተጋላጭ ሀህጻናት መረጃ የሚሠበሠበው በወረቀት ስለነበር የመረጃ ድግግሞሽ እና ምስጢር የመባከን ችግር እንደነበረው ገልጸዋል።

አሁን ግን ችግሩን የቀረፈ አሠራር መበጀቱን እና ሥልጠናም በመሰጠቱ ሥራውን እንደሚያቀልለው ተናግረዋል።

የመተማ ወረዳ ሶሻል ወርከር ሀሃይማኖት እባቡ በበኩላቸው የህጻናትን መረጃ በዘመናዊ መልኩ መሠብሠቡ እና መለዋወጡ የጠራ መረጃ ለማዘጋጀት እና ከውድመት ለመከላከል እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በክልሉ በዘመናዊ መንገድ የችግር ተጋላጭ ለኾኑ ሀህጻናት የጥበቃ አያያዝ ሥርዓት የሚጀመርባቸው ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ገንዳ ውኃ፣ መተማ እና ምዕራብ በለሳ ወረዳ ናቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለማቋቋም እየተሠራ ነው።
Next articleየግብርና ሥራዎች በሜካናይዜሽን የተደገፉ መኾናቸው የተሻለ ምርት ለማምረት እንደሚያግዝ ተገለጸ።