በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለማቋቋም እየተሠራ ነው።

38

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሥራ አሥፈጻሚዎች እና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በቢዝነስ የአመራር ጥበብ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አሥፈጻሚ ብሩክ ታየ (ዶ.ር) ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የልማት ድርጅቶች መሪዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች ትርፋማ እና ውጤታማ እንዲኾኑ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።

የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች አሥተዳደር ዳይሬክተር አበባው ጌቴ የልማት ድርጅቶችን በተሻለ መንገድ ለመምራት የሚያስችል የሥልጠና ሂደት መኾኑን ተናግረዋል። የልማት ድርጅቶች ትርፋማ እንዲኾኑ የተሻለ አመራር እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተሞክሮ በመውሰድ በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለማቋቋም እና የልማት ድርጅቶችን በተማከለ መንገድ ለመምራት እየተሠራ ነው ብለዋል። ጥናት እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የዛሬው ውይይትም በክልሉ ለሚቋቋመው የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።

የኢንቨስትመንት ሆልዲንጉን ለማቋቋም ጥናቱ እየተጠናቀቀ መኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የክልሉ መንግሥት ውሳኔውን እንዳሳለፈ የክልሉ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እንደሚቋቋምም ገልጸዋል።

በክልሉ 46 የሚደርሱ የልማት ድርጅቶች መኖራቸውንም አመላክተዋል።

የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሲቋቋም የልማት ድርጅቶች የክልሉ የልማት አቅም እንዲኾኑ ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የልማት ድርጅቶች ትርፋማ እንዳይኾኑ እንቅፋት እንደኾነባቸውም አመላክተዋል።

በተበተነ መንገድ ሲመሩ በመቆየታቸው በተማከለ መንገድ ሃብት እንዳያፈሩና ትርፋማ እንዳይኾኑ አድርጓቸው መቆየቱንም ገልጸዋል።

ውጤታማ የኾነ የሰው ኀይል አሥተዳደር እና የፋይናንስ አጠቃቀም እንዲተገበር ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ያለባቸውን ችግር ለመፍታት እንደሚሠራም ገልጸዋል።

አደረጃጀታቸውን ማሻሻል ውጤታማ እንዲኾኑ ያደርጋቸዋልም ብለዋል።

የልማት ድርጅቶች ሲቋቋሙ ትርፍ ላይ ያነጣጠሩ አለመኾናቸው ውጤታማ እንዳይኾኑ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ግን የልማት ድርጅቶች ትርፋማ እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የልማት ክፍተቶችን ከመሙላት ባለፈ አትራፊ ኾነው የክልሉን ዕድገት ማፋጠን አለባቸው ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥት የልማት ድርጅቶች ችግሮቻቸው ተፈትቶ ውጤታማ እንዲኾኑ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

ድርጅቶች ውጤታማ ኾነው ለክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየልማት ድርጅቶች ከኪሳራ ወጥተው ትርፋማ እንዲኾኑ አድርጎ ማደራጀት ይገባል።
Next articleዘመናዊ የሕጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝን ለማጠናከር ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ።