የልማት ድርጅቶች ከኪሳራ ወጥተው ትርፋማ እንዲኾኑ አድርጎ ማደራጀት ይገባል።

37

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ለሥራ አሥፈጻሚዎች እና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በቢዝነስ የአመራር ጥበብ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና የልምድ ልውውጥ መድረክ አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አሥፈጻሚ ብሩክ ታየ (ዶ.ር) ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የልማት ድርጅቶች መሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አሥፈጻሚ ብሩክ ታየ (ዶ.ር) የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሀገር አቀፍ ጥሩ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አትራፊ እንዲኾኑ ለማስቻል መቋቋሙን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የኢንቨስትመንት ሥራዎችንም እየሠራ ነው ብለዋል።

ዛሬ የተደረገው ውይይት በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አደረጃጀት መሠረት እንዲደራጁ እና ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እንደኾነ አስረድተዋል።

የአማራ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በሚል ቅርጽ ማደራጀት በሚገባቸው ጉዳይ ለመምከር መምጣታቸውንም አንስተዋል።

በክልሉ ያሉ የልማት ድርጅቶች በተገቢው መንገድ አደረጃጀት ከተፈጠረላቸው ለሀገር እና ለሕዝብ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ላቅ ያለ መኾኑንም አመላክተዋል።

የልማት ድርጅቶች እንደ ንግድ ተቋም ኾነው ይቋቋማሉ አሠራራቸው ግን አትራፊ ያልኾነ ነው ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው ይህ ደግሞ ለኪሳራ እየዳረጋቸው ነው፤ ከኪሳራ ወጥተው ትርፋማ እንዲኾኑ አድርጎ ማደራጀት ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል መሪዎችም የልማት ድርጅቶች ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ቁርጠኛ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ኢኮኖሚውንም ለማሳደግ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚና ከፍ ያለ መኾኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች ትርፋማ ኾነው እንዲደራጁ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የተቋማትን የፋይናንስ አያያዝ እና አጠቃቀም የኦዲት ቁጥጥር እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።

ለመንግሥት ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት አቅም መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ዘመናዊ የሕጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ተጀመረ።
Next articleበአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለማቋቋም እየተሠራ ነው።