በአማራ ክልል ዘመናዊ የሕጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ተጀመረ።

55

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ ሕጻናት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ለመስጠት በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ በሙከራ ደረጃ ሲተገበር ቆይቷል።

ይህንኑ የዳታ ቤዝ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሐ ግብርም በባሕር ዳር ተካሂዷል።

መርሐ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በሕጻናት ጥበቃ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመጠበቅ እና ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የሕጻናትን መብት እና ደኅንነት ለመጠበቅም የሕጻናት የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ማጠናከር እና ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ ሕጻናት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ለመስጠት በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የዳታ ቤዝ ሥርዓት መዘርጋት የሕጻናት ጥበቃ ሥርዓትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

ይሁን እንጂ በክልሉ የሕጻናት መረጃ አያያዝ ከወረቀት ያልዘለለ እና መብት እና ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ የተደራጀ እንዳልነበረ ነው የገለጹት።

ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱ ይህንን ችግር ፈትቶ የሕጻናት ደኅንነት ጥበቃን ለማሳደግ እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ለችግር ተጋላጭ ሕጻናትን እና ለችግር አጋላጮችን መረጃ ለይቶ ለማስቀመጥ፣ የምላሽ አሰጣጥ ሂደቱንም ለመረዳት እና ወቅቱን የጠበቀ ለማድረግ እንደሚያስችልም ነው ወይዘሮ ብርቱካን የጠቀሱት።

የተጠናከረ የመረጃ ሥርዓት መኖር ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ ያለው የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ወጥነት እና ተጠያቂነት እንዲኖረው እንዲሁም ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀ በማድረግ የሕጻናቱን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው ነው የገለጹት።

ሥርዓቱ ሲተገበር በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ተቋማት መካከል ያለው የመረጃ ቅብብሎሽ ሕጻናት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ ያስችላል።

በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች መረጃውን በዘመናዊ እና በቀላል መልኩ ለመያዝ ያስችላቸዋል።

ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ሕጻናት ለይቶ በመያዝ፣ የድጋፍ ዕቅድ ለማዘጋጀት እና ለመተግበርም ያግዛል ነው ያሉት።

ይህንን የሕጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝ ሥርዓት በሙከራ ትግበራ ደረጃ መቆየቱ እና ወደፊትም በሌሎች የክልሉ ከተሞች እና ወረዳዎች ላይ ለመተግበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል።

የሕጻናት ባለሙያዎችን ጨምሮ በመረጃ አያያዝ ላይ ሥልጠና መሰጠቱን እና የቁሳቁስ ግዢ መፈጸሙንም ኀላፊዋ ገልጸዋል።

የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና አስተዋጽኦ አስፈላጊነትንም ጠቅሰዋል።

የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱን ለመተግበር ድጋፍ ያደረገውን ዩኒሴፍ ኢትዮጵያን አመሥግነዋል።

በዕለቱም የሕጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝ ሥርዓት በይፋ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተወዳዳሪ እና ትርፋማ የልማት ድርጅቶችን መፍጠር አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየልማት ድርጅቶች ከኪሳራ ወጥተው ትርፋማ እንዲኾኑ አድርጎ ማደራጀት ይገባል።