“ተወዳዳሪ እና ትርፋማ የልማት ድርጅቶችን መፍጠር አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

37

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሥራ አሥፈጻሚዎች እና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በቢዝነስ የአመራር ጥበብ ላይ ያተኮረ የአቅም ግምባታ ሥልጠና እና የልምድ ልውውጥ መድረክ እያካሄዱ ነው።

በመርሐ ግብሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አሥፈጻሚ ብሩክ ታየ (ዶ.ር) ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የልማት ድርጅቶች መሪዎች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች እስካሁን ባለው ሂደት በክልሉ ከፍተኛ የልማት አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል። በተለይም የመንግሥትን የልማት ክፍተት በመሙላት፣ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ የክልሉን ገቢ በማሻሻል፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር አገልግሎታቸው ከፍ ያለ መኾኑን ነው ያነሱት። በክልሉ ልማት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ እያስቀመጡ መምጣቸውንም አመላክተዋል።

ነገር ግን የልማት ድርጅቶች መንግሥት እና ሕዝብ በሚጠብቃቸው ልክ እንዲሁም መጠን የመወጣት ክፍተት አለባቸው ብለዋል። ተልዕኳቸውን በመፈጸም ሂደት በተደጋጋሚ ክፍተቶች ሲያጋጥሟቸው መቆየታቸውንም አንስተዋል።

በሚገጥማቸው ክፍተት አብዛኞቹ ትርፋማ ከመኾን ይልቅ ኪሳራ ሲገጥማቸው መቆየቱን ገልጸዋል። በሚፈለገው ልክ ትርፋማ ከመኾን ይልቅ ከመንግሥት ድጎማ ሲጠይቁ፣ መንግሥትን እንደማስያዣ አድርገው ብድር ሲወስዱ መቆየታቸውን ነው ያነሱት። የሥራ ባሕላቸው እና አመራራቸውም ከንግድ እና አትራፊ ድርጅትነት ይልቅ የመንግሥት መደበኛ ተቋማት ባሕሪ የተጠናወታቸው ናቸው ብለዋል።

በአመራራቸው፣ በባለሙያ ሥምሪታቸው እና በተግባር አፈጻጸማቸው ውጤታማነት ክፍተት እንዳለበት ነው የተናገሩት። በዚህ አካሄዳቸው ውድድር በበዛበት ዘመን ተወዳዳሪ መኾን እንደማይችሉ እና የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት ፍላጎት ማሟላት እንደማይችሉ ነው የገለጹት።

ጥልቅ የመፍትሔ ሃሳብ ካልተቀመጠ በስተቀር ሕልውናቸውም የሚያሰጋ ድርጅቶች መኖራቸውን ነው ያነሱት። በንግድ ሥራ አመራር እና ነግዶ ማትረፍ ላይ ተመሥርቶ አደረጃታቸውን ማሻሻል አስፈላጊ ነው ብለዋል። የዛሬው መድረክ ላይ የጋራ ፍላጎታችን ላይ ለመግባባት እና የወደፊት ሥራዎች ላይ የጋራ ሃሳብ ለመያዝ ያስችለናል ነው ያሉት።

ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ልምድ የሚወሰድ እና ወደ ራስ የሚወሰድበት መድረክ መኾኑንም አንስተዋል። ድርጅቶች አመራራቸው የተስተካከለ እና ትርፋማ መኾን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። በልማት ድርጅቶች አደረጃጀት እና ትርፋማነት ላይ የምንግባበበት እና አቋም የምንይዝበት መድረክ ነውም ብለዋል።

ትንንሽ አቅሞችን በማጠናከር የሕዝብ እና የመንግሥትን የልማት ፍላጎት እንዲሸፍኑ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። በሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ እና ትርፋማ የኾኑ የልማት ድርጅቶች መፍጠር አለብን ብለዋል። ተወዳዳሪ የኾኑ ተቋማትን ለመፍጠር ደግሞ ግልጽነት መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት ዓመታት የ23 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ዓባይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኀበር ገለጸ።
Next articleበአማራ ክልል ዘመናዊ የሕጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ተጀመረ።