
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በከልሉ ባለፉት ዓመታት የተሠሩ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች በመስኖ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት፣ በእንስሳት ማድለብ እና በደን ውጤቶች ለአርሶ አደሩ ጥቅም ማስገኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች ላለው የአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር በክልሉ እየተሠራ ያለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ እንቅፋት መፍጠሩን ያነሱት ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) እያጋጠሙ ያሉ የዘላቂነት እና የተጠቃሚነት ችግሮችን ለመፍታት የተፋሰስ ማኅበራትን ማጠናከር እና ሳይንሳዊ አሠራሮችን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ነው ያብራሩት፡፡
ቢሮው በተያዘው በጀት ዓመት ከ9ሺህ በላይ ተፋሰሶችን ለማልማት አቅዷል፡፡ዕቅዱን ለማሳካትም ለዞን እና ወረዳ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
በሥራው የሚሳተፍ የሰው ኀይል የመለየት እና የሥራ መሣሪያ የማዘጋጀት ተግባር መጠናቀቁንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
ዘጋቢ፦ ባለ ዓለምየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!