
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት እየተሠሩ የነበሩ እና አሁን ላይ የተጠናቀቁ የውስጥ ለውስጥ የማሳለጫ መንገዶችን፣ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ሱቆችን እንዲሁም ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከጉብኝቱ በኋላ “ከተማችንን ለመለወጥ እየሠራን ነው፤ የአዲስ አበባ ለውጥ ሃብትን በመቆጠብ እና ለተገቢው የጋራ ልማት በማዋል ለዜጎች ትኩረት በመስጠት እየተተገበረ ያለ ሥራ ነው” ብለዋል።
በሚሠራው ሥራ የከተማዋ ነዋሪዎች ትብብር ጎልቶ የታየበት እና ከከተማ እስከ ፌዴራል ያሉ የመሠረተ ልማት መስሪያ ቤቶች ቅንጅት የተረጋገጠበት እንደኾነ ነው ያብራሩት።
የኮሪደር ልማት ሥራው ትልቅ የመፈጸም ብቃት የታየበት፣ ለየት ያለ የሥራ ባሕልም የተተገበረበት፣ ትብብር እና የመሠረተ ልማት ቅንጅት የተሻሻለበት፣ በርካታ የከተማዋ አካባቢ ያልነበሩ አዳዲስ የመሠረተ ልማት አገልግሎት በአይነት፣ በጥራት እና በውበት ማስተዋወቅ የተቻለበት እንደኾነ ተናግረዋል።
ሥራው ለከተማዋም ኾነ እንደሀገር ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል።
በመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ውስጥ ለውስጥ ተሠርተው የተጎበኙ መንገዶች 13 መኾናቸውን ጠቅሰው ይህም 10 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል ነው ያሉት።
ከዋናው መንገድ ጋር የማገናኘት ሥራውም በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ ነው ያስገነዘቡት።
ፅዳት፣ ውበት እና የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ የሥራው ዋነኛ ትኩረት መኾኑን ገልጸው በዚህም በተለይ በፒያሳ እና አራት ኪሎ ላይ እጅግ ተሳክቷል ነው ያሉት።
የሚለሙት ዋና ዋና መንገዶች ብቻ ሳይኾኑ ውስጥ ለውስጥም ነው ያሉት ከንቲባዋ አሁን ላይ በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ በርካታ የልማት ሥራዎች ስለመሠራታቸው ነው የገለጹት።
በተለይ ከመሬት ውስጥ የተሠራው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራ ዘመኑን የተከተለ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የተላበሰ ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ የዲፕሎማት ከተማ በመኾኗ ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ እና መንገዶችም የነገውን ዕድገት ጭምር እንዲሸከሙ ተደርገው እየተሠሩ መኾኑን ነው ያብራሩት።
አራት ኪሎ እና ፒያሳም የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መነሻ በመኾናቸው ታሪክ እና ቅርስነታቸው ተጠብቆ በመሠራታቸው የቱሪስትን ቀልብ የሚስቡ ድንቅ ስፍራዎች ኾነዋል ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ኢትዮጵያዊያን ከውጭ ልምድ ቢቀስሙም ሢሠሩ ግን “እኛነትን እና ታሪካችንን በሚያጎላ መልኩ በመሥራታችን በሁሉም ዘርፍ ስኬታማ ለመኾን ችለናል” ነው ያሉት።
ሥራዎቹ የንግድ ሥርዓትን በማዘመን ረገድ የንግድ ሱቆች አምሽተው እንዲሠሩ በማመቻቸት የገቢ አቅምን ማሳደግ የሚቻልባቸው አሠራሮች ተዘርግተዋልም ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
የሚሠራው የኮሪደር ልማት ሥራ ገቢን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ለመኾን ያስችላል ብለዋል።
በሥራው አሻራቸውን ላሳረፉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!