
ባህር ዳር: ታኅሳስ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት፣ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና በግልግል ዳኝነት ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የተለያዩ ክልሎች የፍትሕ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ነው። የተለያዩ ክልሎች የሕቦች ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ተሞክሮዎችም በመድረኩ ይቀርባሉ።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ.ር) መድረኩ በተለይም በአማራ ክልል ያሉ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል። ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በፍትሕ እና ዳኝነት ዘርፉ ላይ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት በሕግ ማሻሻል እና በተቋም ግንባታ አወንታዊ ውጤቶች ተገኝተዋል፤ አፋኝ፣ ጨቋኝ እና አግላይ የነበሩ ሕጎችም መሻሻል ታይቶባቸዋል ነው ያሉት። ለአብነትም የጸረ ሽብር ሕጉ፣ የመገናኛ ብዙሐን ሕግ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅ እና የምርጫ ቦርድ ሕጎች መሻሻላቸውን ገልጸዋል።
ከለውጡ በኃላ የተሠሩ ማሻሻያዎች አወንታዊ ውጤት ቢኖራቸውም ከሕዝቡ ፍላጎት እና ጥያቄ አንጻር ሲገመገሙ ግን አሁንም ቢኾን መስተካከል ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ አረጋግጠዋል። የሕዝቡን ጥያቄ እና ምሬት ሊፈታ የሚችል የተደራጀ እና የተጠናከረ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ከክልል እስከ ፌዴራል ድረስ አየተሠራ ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመት የሚተገበር ሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ ተነድፎ እየተተገበረ ስለመኾኑም ገልጸዋል። አማራ ክልል በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖም ሀገር አቀፍ የፍትሕ ማሻሻያ ሥራውን በትጋት እየተገበረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሻሻሉ ከተመረጡት 10 የፍትሕ አምዶች ውስጥ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓትን መዘርጋት አንዱ መኾኑን ጠቁመዋል። በአማራ ክልል የዳበሩ እና ለረጅም ዓመታት ሲተገበሩ የቆዩ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ልምዶች አሉ ብለዋል። መንግሥት ለነዚህ ልምዶች ዕውቅና በመስጠት በአግባቡ እንዲተዳደሩ በማድረግ እና ከሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር በማጣጣም ለመጠቀም ውይይቶች እየተደረጉ ስለመኾኑም አንስተዋል።
ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ሙግቶችን ለመፍታት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው በተለያዩ ጥናቶች ስለመረጋገጡም ሚኒስቴር ዴኤታው አንስተዋል። ብዙዎቹ የሀገራችን አካባቢዎች በባሕላዊ የግጭት መፍቻ የሽምግልና ሥርዓት ለመዳኘት ፍላጎት እንዳላቸው በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በጥናት ስለመረጋገጡም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም እነዚህን እሴቶች በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ አካትቶ ለመጠቀም የሚያስችል ውይይት ማዘጋጀቱ እንደሚያስመሰግነው ገልጸዋል። አስማሚነት እና የግልግል ዳኝነትም የፍርድ ቤቶችን ጫና የሚቀንሱ፣ ወጭ ቆጣቢ እና ቀልጣፋ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል። እነዚህ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግም ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
የተጀመረው የለውጥ ሥራ ከዳር ደርሶ የሕዝቡ የፍትሕ አገልግሎት እንዲሻሻል ለማድረግ ፍትሕ ሚኒስቴር አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ዶክተር ኤርሚያስ አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!