
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የመስኖ ዘር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጫጫ ክፍለ ከተማ ተጀምሯል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ ግዛት አብዩ ክልሉ ለግብርና ልማት በሰጠው ትኩረት በበጋ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሠራ ነዉ ብለዋል። በክልሉ 254 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዘርፉ የሚሰማሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የድጋፍና ክትትል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነዉ ያሉት። የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ከተማ አሥተዳደሩ ከከተማ አገልግሎት በተጨማሪ በግብርና አማራጮችም ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ መርሻ አይሳነው በዓመቱ ለመስኖ ልማት የሚውሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በስፋት ለመጠቀም ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በመስኖ ልማት 2 ሺ 294 ሄክታር በመስኖ ለማልማት እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል። በመስኖ ከሚለማዉ መካከል 1 ሺ 500 ሄክታር የሚሆነው በበጋ መስኖ ስንዴ የሚለማ መኾኑን ገልጸዋል። ለመስኖ ልማቱ ከ7 ሺ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እና 2 ሺ 250 ኩንታል ምርጥ ዘር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ውኃን በአግባቡ ለመጠቀም 163 የውኃ መሳቢያ ፓምፖች ጥቅም ላይ እየዋሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጫጫ ክፍለ ከተማ የሚገኙ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማቱ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!