ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በሜካናይዜሽን የታገዘ የግብርና ሥራ እየተተገበረ ነው።

54

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በሜካናይዜሽን የታገዘ የግብርና ሥራ እየተተገበረ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ መሪዎች እና የግብርና ባለሞያዎች በተገኙበት የግብርና ሥራዎች ግምገማ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በክልሉ የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል። የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በሜካናይዜሽን የታገዘ የግብርና ሥራ እየተተገበረ መኾኑንም ገልጸዋል። ከመኽር የግብርና ሥራዎች በተጨማሪ የበጋ መስኖ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

በበጋ ስንዴ ልማት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው በዚህ ዓመትም የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል። የመስኖ ልማት፣ የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የሌማት ትሩፋት፣ የተቋም ግንባታ እና ከተረጅነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ሥራዎች ርብርብ የሚደረግባቸው መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮምዩኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በክልሉ በበጋ መስኖ በ254 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በማልማት 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ190 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ሰሊጥ ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።
Next articleወጣቶች የሙስና ወንጀልን በመከላከል የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።