
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን 190 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ሰሊጥ ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል። በመምሪያው የግብይት ባለሙያ ጌታቸው ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ ዓመት ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ ነው።
ከጥቅምት 20/2017 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ የሰሊጥ ግብይት 190 ሺህ 980 ኩንታል በአቅራቢዎች፣ በውልና ኢንቨስትመንት ላኪዎች እና በኅብረት ሥራ ማኅበራት ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ ከ160 ሺህ ኩንታል በላይ የሚኾነው በውል እና በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ እና የላኪ ፈቃድ ባላቸው ባለሃብቶች በቀጥታ ወደ ውጭ የሚላክ መኾኑን ገልፀዋል።
ግብይቱም በአካባቢው ቀደም ሲል በተቋቋሙ 15 የአንደኛ ደረጃ ገበያ ማዕከላት መፈፀሙን ነው የተናገሩት። ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ ያለውን የሰሊጥ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እየተሰራ መኾኑን ተናግረዋል። የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላትን የመቆጣጠሩ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የጉማውንት ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስፈጻሚ መላክ ትዕዛዙ እንዳሉት ድርጅታቸው ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን ሰሊጥ በመግዛት ወደ ውጭ ይልካል። በዚህ ዓመት ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ወደ ውጭ ለመላክ አቅደው እስካሁን ከ8 ሺህ ኩንታል በላይ ከማዕከላዊ ገበያ በመግዛት ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መኾኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የሰላሙ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ ያቀዱትን ያክል ሰሊጥ ለመግዛት የሚያስችላቸው መኾኑን ጠቅሰው ጥራት ያለው የሰሊጥ ምርት በበቂ መጠን እየቀረበ መኾኑንም አመልክተዋል። በመተማ ወረዳ በኮኪት አንደኛ ደረጀ የገበያ ማዕከል አቅራቢ ነጋዴ አቶ ሙሐመድ ሀሰን በበኩላቸው የሰሊጥ ምርት ጥራቱ የተሻለ በመኾኑ ተፈላጊነቱ መጨመሩን ነው የተናገሩት።
በዚህ ዓመት እስከ 3 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ አቅደው እየሰሩ መኾኑን ገልጸው እስካሁን የ1 ሺህ 200 ኩንታል ሰሊጥ ግብይት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!