በጤና ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምርምር አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡

60

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባዔ እየተካሄደ ነው። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 3ኛው ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባኤ በባሕርዳር እየተካሄደ ነው። ጉባኤውን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ያዘጋጁት ነው። ጉባዔው “ፅኑ የጤና ሥርዓት ለኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ” በሚል መሪ መልዕክት ለቀናት የሚካሄድ ነው።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስትቲዩት ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የጤና ምርምር ጉባኤው እንደ ክልል እና እንደ ሀገር ያሉ የማኅበረሰብ ጤና ችግሮችን መፍታት እንደሚያስችል ነው ያመላከቱት፡፡ ዘላቂና እና ፍትሐዊ የጤና ሥርዓትን መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የጤና ስርዓቱን ዘላቂና ፍትሐዊ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡

ለማኅበረሰቡ ዘላቂ የጤና ስርዓትን ለመገንባት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅም አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የአደጋ ጊዜ ምላሽ፣ የጤና ምርምር ሥራ፣ የላቦላቶሪ አቅምን የማጠናከርና የመገንባት፣ የጤና መረጃ ትንተና ሥራዎችን እና ሌሎችን እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

በጤና ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምርምር አስፈላጊና ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በማስረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔና ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡ ተግዳረቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ ጠንካራና የማኅበረሰብ ጤና መገንባት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ሰብሳቢ እና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ንጉሥ ታደሰ (ዶ.ር) ፎረሙ ለኅብረሰተብ ጠቃሚ የኾኑ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ከሕዝባቸው ጋር መቆማቸውንም ገልጸዋል፡፡ ፎረሙ ከአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ጋር በመኾን የወባ ወረርሽኝ ለመግታትና በሌሎች ጉዳዮችም መሥራቱን ነው የተናገሩት፡፡

ተቋሙ ገለልተኛ እና ከፖለቲካ አመለካከት ነጻ ኾኖ ሲቋቋም ዋናው ዓላማው ለሕዝብ የሚጠበቅበትን ለማድረግ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ ለማኅበሰረብ ተጠቃሚነት ከአጋር አካላት ጋር በመኾን እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ጉባኤው ለጤና ችግሮች መፍትሔ የሚያመላክትና እና አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያስችል መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የጤና ምርምር ጉባኤው አሁን ላይ በችግር ያለውን የጤና ችግር ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡ በወረርሽኝ፣ በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ችግር መኖሩን ያነሱት ኃላፊው የጤናውን ዘርፍ በምርምር መደገፍ የማይበገር የጤና ስርዓትን ለመገንባት ያስችላል ነው ያሉት፡፡ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጤናውን ዘርፍ በእጅጉ እደጎደው ነው የተናገሩት፡፡ የጤና ግባቶችን በተሟላ መንገድ ለማቅረብ፣ የወባ ወረርሽኝን በነጻነት ተንቀሳቅሶ ለመከላከል ፈተና መኾኑንም አንስተዋል፡፡

መንግሥታዊ የኾኑና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት አሁን ካለው ችግር ለመውጣት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የጤና ምርምሮችን ማድረግ የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ምርምር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም አመላክተዋል፡፡ የኅብረሰተብ ጤናን ለመጠበቅ ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረሰተብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በምርምር የተደገፈ ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በተላላፊ በሽታዎችና የተፈጥሮ አደጋዎች ላይም ምላሽ እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ የዜጎችን ጤና ሊጠበቅ የሚችል ሥራ እንደሚሠሩም አመላክተዋል፡፡

ጥራት ያለው የላቦላቶሪ አገልግሎትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡ በጤና ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ትልቅ ጥቅም እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ የምርምር ግኝቶችን ወደ ተግባራዊ መፍትሔዎች መቀየር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የኅብረሰተብ ጤናን ለመጠበቅ በትብብር እና በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት ምርምር አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በጤናው ዘርፍ ፈታኝ ጊዜያት እንደታለፉ የተናገሩት ሚኒስትሯ ከአስቸጋሪ የኮሮና ቫይረስና ይዟቸው ከመጣቸው የጤና ችግሮች ወጥተን እዚህ ደርሰናል ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ስኬታማ ሥራዎችን መሥራቷንም አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ፣ በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መፈተኗንም አስታውሰዋል፡፡

የጤና ችግሮችን በምርምር መፍታት ግዴታ እና አስፈላጊ እንጂ ቅንጦት አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ምርምር የጤና ስርዓቱን ለመቀየርና የኅብረተሰብን ጤና ለመጠበቅ እንደሚያስችልም አንስተዋል፡፡ የጤና ስርዓቱን ለመቀየር ብዙ መሠራቱን ያስታወሱት ሚኒስትሯ አሁንም ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ይቀሩናል ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የጤና ስርዓቱን ለማዘመን እና ጠንካራ የጤና ስርዓርት ለመገንባት ቁርጠኛ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

የጤና መሠረት ልማቶችን እና ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ የጤና ስርዓቱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ በጤና ስርዓቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና ለማዘመን ፈተናዎች ሊገጥሙን ይችላሉ ነገር ግን መቀየር እንችላን ነው ያሉት፡፡ በጋራ መሥራት ከተቻለ ጠንካራ የጤና ተቋማትን መገንባት እንደሚቻልም አስታውቀዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአማራ ክልል የዳበረ የግጭት አፈታት ባሕል ያለው መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ገለጹ።
Next articleከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ሕጻናትን መመለስ እና ትውልድን ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ።