
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት፣ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና በግልግል ዳኝነት ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በውይይቱ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው በአማራ ክልል የዳኝነትና አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓትን ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል። የተደረጉ ማሻሻያዎች ያስመዘገቧቸው ተጨባጭ ውጤቶች አሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ የተገልጋዩን ፍላጎት ማርካት የሚችል ውጤታማ የፍትሕ ሥርዓት በመዘርጋት በኩል ግን ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
የተገልጋዮችን ፍላጎት ለማርካት ከመለስተኛ ማሻሻያዎች ወጥቶ መሠረታዊ የማሻሻያ ሥራ ማከናወን አስፈላጊ ነው ብለዋል። ይህን ለማድረግም ሀገር አቀፍ የፍትሕ ሥርዓት ለውጥ እቅድ ወጥቶ ለውጥ የሚያስፈልጋቸው አምዶችም ተለይተው ወደ ትግበራ ተገብቷል ነው ያሉት።
አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል አንዱ የለውጥ ሥራው ትኩረት መኾኑንም አመላክተዋል። ይህንን አሠራር ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ጋር በማስተሳሰር ወይም ደግሞ ራሱን አስችሎ ሥራ ላይ በማዋል የተቀላጠፈ የፍትሕ ሥርዓትን እናረጋግጣለን፤ የተገልጋዩን ፍላጎትም እናረካለን ነው ያሉት።
አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ጥቅም ላይ ሲውሉ ከቅልጥፍና ባሻገር እውነትን ለማውጣት፣ በደል እና ቁርሾዎችም በትክክል እንዲያሽሩ ለማድረግ እና ጉዳቶችም እንዲጠገኑ እንደሚያስችል አብራርተዋል።
አማራ ክልል በየአካባቢው የዳበረ እና ቱባ የግጭት መፍቻ ሥርዓት አለው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህንን ከሀገር እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች አኳያም በማየት ጥቅም ላይ ለማዋል መሥራት እንደሚገባ ነው ያመላከቱት። ሥርዓቱን ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ውይይት እንደሚደረግበትም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!