“ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጠንካራ አመኔታ እንዲኖራቸው የሚያስችል የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት እንሠራለን” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

29

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት፣ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና በግልግል ዳኝነት ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የፍትሕ ሚኒስትር ድኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃንን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎችም የክልሉ መሪዎች፣ የተለያዩ ክልሎች የፍትሕ ተቋማት መሪዎች፣ ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እየተሳተፉ ነው።

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ “ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጠንካራ አመኔታ እንዲኖራቸው የሚያስችል የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት እንሠራለን” ብለዋል። ክልሉ የካበቱ የባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓቶች ባለቤት መኾኑንም አንስተዋል። ባሕላዊ እሴቶችን ከፍርድ ቤቶች የፍትሕ ሥርዓት ጋር በማቀናጀት የሕዝቡን የፍትሕ ጥያቄዎች መመለስ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ያልተጠኑ እና በውል ያልተለዩ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን በጥናት እና ምርምር በመደገፍ ማውጣት እና ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በአማራ ክልል ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት ሲሠራ ቆይቷል ያሉት አፈ ጉባዔዋ አሁንም ቢኾን ቀሪ ሥራዎች አሉ ነው ያሉት። ሕዝቡ ፍርድ ብቻ ሳይኾን ከእውነት የመነጨ ፍትሕ እንዲያገኝ፣ ለፍትሕ ያለው አመኔታም ከፍ እንዲል ተከታታይ ሥራዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።

የክልሉ የፍትሕ ተቋማት በክልሉ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ኾነው እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። አሥተማማኝ የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት ደግሞ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ የሽምግልና ሥርዓቶችን በተገቢው ሁኔታ አጎልብቶ መጠቀም ተገቢ ነው ብለዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባሕላዊ ሽምግልናን በማጎልበት የሕዝቡን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።
Next articleአማራ ክልል የዳበረ የግጭት አፈታት ባሕል ያለው መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ገለጹ።