ተመድ የአንካራው ስምምነት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችል መልካም እርምጃ መሆኑን ገለጸ።

24

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት የአንካራው ስምምነት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችል መልካም እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል። በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተርኪዬ አደራዳሪነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የደረሱበትን ስምምነት አድንቋል። የተቋሙ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች በወዳጅነት እና በመከባባር መንፈስ የተደረገው ውይይት መልካም ጅማሮ እንደሆነ ገልጸዋል። በቀጣይ የሚካሄደው የቴክኒካል ውይይት የተሻለ ውጤት ይዞ እንደሚመጣ እምነቴ ነው ብለዋል።

ተርኪዬ ሀገራቱ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለተወጣችው ሚና ያደነቁት ቃል አቀባዩ፤ ተመድ የውይይት ሂደቱን በየትኛውም መንገድ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በቱርኪዬ አደራዳሪነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የደረሱበትን ስምምነት አድንቃለች። የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምምነቱ ተግባቦት እና ውይይትን ለማጠናከር የሚያስችል ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጾ፤ በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ገንቢ ትብብር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል ብሏል።

ውይይቱ በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ የተወሰደ በጎ እርምጃ መሆኑንና ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቆሞቻቸውን ባከበረ መልኩ እንዲለሙና እንዲበለጽጉ በር እንደሚከፍት አመልክቷል። ሚኒስቴሩ ተርኪዬ ለአንካራው ስምምነት ለተወጣችው የአደራዳሪነት ሚና አድናቆቷን ገልጿል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያና ሶማሊያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻ የገለጸች ሲሆን በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እንደምትሠራም አስታውቃለች። በተያያዘም የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአንካራ ስምምነት ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ መረጋጋትን ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ እርምጃ ነው ሲል ገልጿል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውይይታቸውን በመተማመን የአጋርነት መንፈስ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ ሰላም ለመገንባት እና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሁሉም ድርሻ ወሳኝ ነው።
Next articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።