“ቅንጅትና ትብብር ለጤናው ዘርፍ አስፈላጊ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

48

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 3ኛው ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባኤ በባሕርዳር እየተካሄደ ነው። ጉባኤውን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ያዘጋጁት ነው።

ጉባዔው “ፅኑ የጤና ስርዓት ለኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ” በሚል መሪ መልዕክት ለቀናት የሚካሄድ ነው። በጉባዔው ላይ መልእክት ያስተለፉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ማኅበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሕዝብን ሁለንተናዊ ጤና ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። ዜጎች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጤናቸው ተጠብቆ አምራች ዜጋ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የጤና ሥርዓቱ ነገን ታሳቢ ያደረገ፣ ዛሬንም የዋጀና ችግሮችን መቋቋም የሚችል ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል። በጤናው ላይ የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለማስፋት ምርምር እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት። የጤና ሥርዓቱ አይበገሬ ተብሎ የሚወሰደው በግጭት ውስጥ ምላሽ ስለሰጠ ብቻ ሳይኾን ከግጭት ባሻገር ነገርን አልሞ ሲሰራ ነው ብለዋል። ነገን ታሳቢ ያደረገ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የጤና ምርምር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በተለይም የእናቶች እና የሕጻናት ጤና እንክብካቤ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መኾኑን ነው ያመላከቱት። የጤና ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል። የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤና መጠበቅ የነገዋን ሀገር መሥራት እና ነገ ላይ ተወዳዳሪ የኾነ ትውልድን መፍጠር ነው ብለዋል።

የጤና ሥርዓቱ በምርምር ይታገዝ ሲባል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን ማከም የምንችልበትን የፋይናንስ ሥርዓትን መገንባትን ታሳቢ ያደረገ መኾን አለበት ነው ያሉት። የሥነ ሕዝብ እድገት ጤናማ እና ውጤታማ እንዲኾን፤ የሕክምና ግብዓት አቅርቦት የተሟላ እንዲኾን በምርምር መታገዝ ይገባዋልም ብለዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ባሕላዊ ዕውቀቶች አሉን ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ቀድመን የጻፍናቸው፣ የተመራመርናቸው ምርምሮች አሉን፣ ነገር ግን ወደ ጥቅም የመቀየር ክፍተቶች አሉብን፣ ምርምሮች ባሕላዊ ዕውቀቶችም ታሳቢ ያደረጉ መኾን አለባቸው ብለዋል።

ባሕላዊውን ዕውቀት ከዘመናዊ ጋር ማገናኘት ከተቻለ የኅብረተሰብን የጤና ችግር መፍታት ይቻላል ነው ያሉት። ቅንጅትና ትብብር ለጤናው ዘርፍ አስፈላጊ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ትብብር እና ቅንጅት አቅምን ያከማቻል፣ ወረት ይሰበሰባል ነው ያሉት። ቅንጅት እና ትብብር በሁሉም ቦታ ያሉ አቅሞችን አሰባስቦ ለመጠቀም ወሳኝና አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ለሕዝብ ፈጣንና ወቅታዊ የጤና ምላሽ ለመስጠት ቅንጅትና ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት። ምርምር በራሱ ቅንጅትና ትብብር እንደሚሻም አመላክተዋል። በተለይም በዚህ ወቅት የሁሉም ቅንጅታዊ አሠራር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ጋር በክልሉ የጤና ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ነው።
Next articleአፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት እንደሚሠሩ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አስታወቁ።