
ገንዳ ውኃ: ታኅሳስ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ “የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚናን በማጉላት አካታች ዘላቂ ልማትን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል የአካል ጉዳተኞች ቀን በገንዳ ውኃ ከተማ ተከብሯል። መርሐ ግብሩን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ እና የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት በጋራ በመኾን ነው ያዘጋጁት። በመድረኩ ላይ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል አቶ አሚር አሊ እንዳሉት ማኅበረሰቡ ስለአካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት የተስተካከለ እንዳልኾነ ገልጸዋል። አካል ጉዳተኞች እንደማንኛው ሰው መሥራት እንደሚችሉ እና እምቅ አቅም እንዳላቸውም ጠቁመዋል። አካል ጉዳተኞችን በኢኮሚያዊ እና በማኅበራዊ ኑሮ በማገዝ የተሻለ ሥራ እንዲፈጥሩ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ መቶ አለቃ ክንዴ አረጋ እንደተናገሩት አካል ጉዳተኝነት አያስገልልም ስለኾነም ለማኅበረሰቡ ስለአካል ጉዳተኝነት ግንዛቤ እና ዕውቅና መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት። አካል ጉዳተኞች ማንኛውንም ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ነው ያስገነዘቡት። ቤት ለቤት ተደብቀው ያሉ አካል ጉዳተኞችን ወደ አደባባይ እና ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ ለአካል ጉዳተኞች ማኅበር ድጋፎች እየተደረጉ እንደኾነ ገልጸዋል። ለግንባታ የሚውል 1 ሺህ 460 ካሬ ሜትር መሬት ተሰጥቷል፤ በተጨማሪም የ400 ሺህ ብር ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል። ረጅ ድርጅቶችን እና ባለሃብቶችን በማስተባበር ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የወረዳው የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ መምህር ጌታ ታደሰ አካል ጉዳተኞች ባለተሰጥኦ እና የብሩህ አዕምሮ ባለቤት ናቸው፤ ከረዳናቸው እና ከተንከባከብናቸው እንደሌሎች መሥራት ይችላሉ ብለዋል። የዊልቸር እና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸውም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት እማኘው አካል ጉዳተኞችን በማካተት እና ከጎናቸው ለመኾን በጋራ እንሠራለን ብለዋል።
መምሪያ ኀላፊዋ አካል ጉዳተኞች ከልመና እና ከጥገኝነት ተላቅቀው ራሳቸውን ችለው እንዲሠሩ መደገፍ እና መንከባከብ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!