የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባዔ እያካሄደ ነው።

34

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 3ኛው ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው። ጉባኤውን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ያዘጋጁት ነው።

ጉባዔው “ፅኑ የጤና ሥርዓት ለኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ” በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄድ ነው። በጉባዔው ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ምሁራን ተገኝተዋል።

በጉባዔው ተመራማሪዎች አዳዲስ የምርምር ሃሳቦችን እና ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎች ለወጣት ተመራማሪዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት፣ የሃሳብ መለዋወጥ እና የግንኙነት መረብ መፍጠር ዓላማ አድርጎ የሚካሄድ መኾኑም ተገልጿል።

በዚህ ችግር ወቅት ተደራሽ ላልኾኑ ሰዎች ችግራቸውን ለመፍታት ውይይት የሚደረግበትና ምክረ ሃሳብ የሚመነጭበት ጉባኤ ነው ተብሏል።

አሁን ያለውን የተወሳሰበ የኅብተሰብ ጤና ችግር መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድም ተመላክቷል። ፍትሐዊ የኅብረተሰብ ጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንዲኖር የመፍትሔ ሃሳቦች እንደሚቀርቡም ይጠበቃል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሥምምነቱ ሀገራችን በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርገው ጥረት የጎላ ሚና ይጫዎታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleግብርና ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የጥጥ ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት ተፈራረመ።