“ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መልእክት በላሊበላ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

30

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ቅርስ የሆነው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መገኛ የሆነችው የላሊበላ ከተማ ሕዝብ ዓላማው ሰላምን ማስፈን የሆነ ሰልፍ እያካሄደ ነው።

የኑሮ መሠረቱ እና ኅልውናው በቅርሱ ላይ የተመሠረተው የላሊበላ ሕዝብ ቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነት አሁን ደግሞ ባለው ሰላም ማጣት ለረሃብ እና ለችግር እየተዳረግን ነው በሚል ጦርነት ይብቃ፣ ሰላም እንፈልጋለን ፣ ማንም ማንንም አይግደል መገዳደል ይቁም ብሎ ሰልፍ ወጥቶ ሰላም እንዲሰፍን መንግሥትንና የሚመለከተውን ሁሉ እየጠየቀ ነው።

መጪውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እና የቅዱስ ላሊበላን ልደት በአንድ ጊዜ የምታከብረው ላሊበላ ይህ ወቅት በሀገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች የምትጎበኝበት ነዋሪውም የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን የሚሸምትበት ገቢ የሚያገኝበት መሆኑ ይታወቃል።

ነገር ግን በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ችግር ላይ በመውደቁና ተስፋው የሆነውን ይህንን በዓል ለማክበር ወጥቶ ሠርቶ ለመግባት ሰላም እንዲረጋገጥለት እንደሚፈልግ በሰልፍ እየጠየቀ ይገኛል።

የከተማዋ ነዋሪዎች የሰላም ምልክት የሆነውን ነጭ ሰንደቅ እያውለበለቡ የሚከተሉትን ሃሳቦች አሰምተዋል፦

👉 ላሊበላ ጦርነት የሚገባት ከተማ ሳትሆን ሰዎች በጸሎትና ምህላ የሚኖሩባት ትሁን
👉 አሁናዊ የጦርነት ችግሮች በውይይት ይፈቱ
👉 ሰው መሞት የለበትም ደም አፋሳሽ ጦርነት ይብቃ
👉 በጦርነት ምክንያት ችግር ውስጥ ነን
👉 ላሊበላ ሰላምን እንጅ ጦርነትን አትፈልግም።
👉 ጦርነት ይቁም በተቀደሰ ቦታ የተቀደሰ ሥራ ብቻ
👉 ሰላም ከሌለ መማርም ሆነ መታከም የለም
👉 ስለሕዝብና ስለሀገር ሲባል ችግሮች በንግግር ይፈቱ
👉 የከተማችን እስትንፋስ ሰላም ነው
👉ሰላም ቱሪዝም ነው ቱሪዝም ሰላም ነው የሚሉና ሌሎችንም መልእክቶች ተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ባሕር ዳር ገቡ።
Next article“ሥምምነቱ ሀገራችን በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርገው ጥረት የጎላ ሚና ይጫዎታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ