
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አደራዳሪነት በአንካራ ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ድርድር ሁለቱንም ሀገራት በሚያግባባ ስምምነት ተጠናቅቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ግብዣ ዛሬ ምሽት በአንካራ ውይይት አድርገዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ውይይቱን ካደረጉ በኋላም በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
መሪዎቹ በመግለጫቸውም፤ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በኩል ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አማራጭ በምታገኝበት አማራጭ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር መስማማታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመግለጫቸው፤ ቱርክ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ለምታደርገው ከፍተኛ አስታዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያና የሶማሊያ ሕዝቦች በቋንቋ፣ በባህል እና በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጋራ ሰላምና ልማት ከሶማሊያ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በበኩላቸው፤ የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ ሰላም የከፈሉትን መስዋዕትነት አይዘነጋም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በቀጣይም ሰላምን ለማፅናት በሚያደረጉት ጥረት መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሀገራት የፈረሙት ሰነድ ትብብርን፣ የኢኮኖሚ እድገትን እና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!