የጤና ችግሮችን በምርምር ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

61

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ጉባኤ በባሕርዳር ሊያካሂድ ነው። ጉባዔው የተዘጋጀው በአማራ ክልል ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ጋር በጋራ በመተባበር ነው። 3ኛው ዓመታዊ የጤና ምርምር ጉባዔ “ፅኑ የጤና ሥርዓት ለኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ” በሚል መልዕክት ከታኅሳስ 3 እስከ 5/2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል ነው የተባለው።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ጉባዔውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል የጤና ምርምር ልማትን በማጠናከር ለውሳኔ ሰጭ አካላት ማቅረብ፣ የምርምር ውጤቶችን በማመንጨት የጤናው ስርዓት የተሻለ እንዲኾን ማድረግ ነው ብለዋል።

የጤና ፕሮግራሞች የበለጠ እንዲሻሻሉ ማድረግ፣ ፈጠራን እና ቴክኖሎጅ ሽግግርን በጤናው ዘርፍ ለማጠናከር እንደሚሠራም ተናግረዋል። በየዓመቱ የምርምር ጉባዔ እንደሚካሄድ የገለጹት ዳይሬክተሩ ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰቡን የጤና ችግር በመለየት የመፍትሔ ሃሳብ የማመንጨት ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል።

ከዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የምርምር ተቋማት፣ ከረጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ምርምር ማካሄድ ኢንስቲትዩቱ በደንብ ከተሰጡት ተግባራት መካከል መኾኑንም አንስተዋል። ጉባዔው በባለፉት ዓመታት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ሲካሄድ እንደነበረ ያነሱት ዳይሬክተሩ የዘንድሮው ጉባኤ በአማራ ክልል ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ጋር በጋራ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በጉባዔው ተመራማሪዎች አዳዲስ የምርምር ሃሳቦችን እና ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ብለዋል። ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎች ለወጣት ተመራማሪዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት፣ የሃሳብ መለዋወጥ እና የግንኙነት መረብ መፍጠር ዓላማ አድርጎ የሚካሄድ መኾኑንም ገልጸዋል።

ጉባዔው “ፅኑ የጤና ሥርዓት ለኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ” በሚል መሪ መልእክት የተዘጋጀ መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ በዚህ ችግር ወቅት ተደራሽ ላልኾኑ ሰዎች ችግራቸውን ለመፍታት ውይይት የሚደረግበትና ምክረ ሃሳብ የሚመነጭበት ጉባኤ ነው ብለዋል።

አሁን ያለውን የተወሳሰበ የኅብተሰብ ጤና ችግር መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድም አመላክተዋል። ፍትሐዊ የኅብረተሰብ ጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንዲኖር የመፍትሔ ሃሳቦች እንደሚቀርቡም ተናግረዋል።

ጉባዔው በተሳካ መንገድ እንዲካሄድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል። ምርምር የቅንጦት ሥራ አለመኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በችግር ጊዜ መፍትሔ የሚፈልቅበት፣ የሰዎችን ሕመምና ሞት ለመቀነስ ሃሳብ የሚፈልቅበት ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተሉ መኾኑ ተጠቆመ።
Next articleኢትዮጵያ በሶማሊያ ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አማራጭ በምታገኝበት አማራጭ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር መስማማት ላይ ተደረሰ።