ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተሉ መኾኑ ተጠቆመ።

162

ደብረ ብርሃን፡ ታኅሳስ 2/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂደዋል። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንደ ሀገር የሚያደርሱት ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚ ጫና ከፍተኛ መኾኑን የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናግረዋል።

ዋና አፈ ጉባኤዋ ድርጊቱን ከመከላከክ ጎን ለጎን ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት አንዱ መፍትሄ ነው ብለዋል። የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሁሉም እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል። ድርጊቱን መድረክ ላይ በምናወግዘው ልክ በተግባር ሠርተን ማሳየት አለብንም ብለዋል።

በተለይ በቅርቡ ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲባባሱ ምክንያት እየኾነ ነው ተብሏል። ቀደም ብለሎም ተጠያቂነት ላይ የሚስተዋለው ውስንነት የጸጥታ ችግሩ ሌላ መሸሸጊያ እየኾነው መጥቷልም ብለዋል። በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ትምህርት የጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን ማስወገጃ ዋነኛ መሳሪያ ቢኾንም አሁን ላይ በክልሉ 4 ነጥብ 9 ሚሊየን ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋልም ብለዋል።

ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ በመኾናቸው ለሕገ ወጥ ስደት፣ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለጾታዊ ጥቃት ጭምር እያጋለጣቸው መኾኑን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት በጥቃት ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ከተሳታፊዎች ተነስቷል።

በሀገራችን የሚፈጸሙ ጎጆ ልማዳዊ ድርጊቶች አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርትን አራት በመቶ ይቀንሳሉም ተብሏል።

ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከመንግሥት ጎን በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላም እንደሚያስከብሩ የመካነ ሰላም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next articleየጤና ችግሮችን በምርምር ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።