ከመንግሥት ጎን በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላም እንደሚያስከብሩ የመካነ ሰላም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

39

ደሴ፡ ታኅሳስ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” የነዋሪዎች ውይይት በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ አሥተዳደርና እና በቦረና ወረዳ ተካሂዷል። በውይይቱ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳደሪ አሊ መኮንን ፣ በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኘው ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የቀበሌ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በወረዳው በተከሰተው የሰላም መደፍረስ በርካታ ጉዳቶች መድረሳቸውን ተናግረዋል ፡፡ ሰላምን አጥብቀን እንሻለን ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች ሰላምን ማስፈን ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑና ስለማይሳካም ጭምር በራሳችን የአካባቢያችንን ሰላም እናስከብራለን ብለዋል፡፡
የሰላም ውይይቱ ተሳታፊዎች፦

👉የሰላም ውይይቱ እስከ ቀበሌ ይውረድ ፣
👉አሁንም የሰላም ጥሪ ተደርጎ በጫካ ያሉ የኛው ልጆች እንዲገቡ ይደረግ ፣
👉ሰላማችንን አስከብረን ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ ልጆቻችን ይማሩ ፣
👉የታጠቁ ኀይሎች የሚኖሩት የሚበሉት የሚጠጡትም በሕዝቡ ውስጥ ስለሆነ የሚገሉት፣ የሚዘርፉት ሕዝቡን በመሆኑ በአዳራሽ የምንናገረውና በውጭ የምንሠራው የተስማማ ይሁን ፣
👉ልባችን ከምላሳችን ይስማማ ይህ ሲሆን ሰላም ይሰፍናል ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም “በክልሉ ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው የዘራፊዎች ስብስብ በአቋራጭ ሀብት ለማጋበስ ፣ የራሱን ወገን እየገደለ፣ እያገተ ገንዘብ የሚቀበል ፣ ትምህርት ቤትን የዘጋ ስብስብ እንጂ የአማራን ጥያቄ የማስመለስ ፍላጎትም፣ አቅምም፣ የፖለቲካ ዝግጁነትም የሌለው ተራ የዘራፊዎች ስብስብ መሆኑን ሕዝቡ ሊገነዘብ ይገባል” ብለዋል፡፡

“ጀግናው የቦረና ሕዝብ በነዚህ ዘራፊዎች መታለል የለበትም፣ መንቃትና በቃህ ማለት አለበት” ነው ያሉት ሌትናንት ጄኔራል በላይ ስዩም ፡፡ በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኘው የቦረና ሕዝብ በሕገወጦች መሰቃየት የለበትም በቃኝ ማለት ይገባዋል ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ራሱ ሰላሙን ማረጋገጥ አለበት የሕዝቡ ሰላም የሚረጋገጠው በራሱ በሕዝቡ ተሳትፎ ነው ነው ያሉት፡፡

በወረዳው አደረጃጀት ፈጥረው ሰላም ማስከበር የቻሉ ቀበሌዎችን ተሞክሮ ወደሌሎች በማስፋፋት የወረዳውን ሰላም ማስከበር ይገባል ያሉት አቶ ተስፋ ከሕዝቡም ሆነ ከአመራሩ ውስጥ ለፅንፈኛና ዘራፊዎች የመረጃና ሌሎች ድጋፎችን እየሰጡ የሚገኙትን በመምከር ፤ ካላረፉ ደግሞ ለፀጥታ ኀይሎች አሳልፎ መስጠት አለባችሁ ብለዋል፡፡

በአካባቢው ሰላምን አረጋግጡ የተነሱ የልማት ጥያቄዎችን በየደረጃው መልስ እንዲሰጡ እንሠራለን ብለዋል አቶ ተስፋ፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አሊ መኮንን “ዘራፊ ቡድኖች ለአማራ ሕዝብ ጥቅም ነው የሚለው ትግላቸው የትም የማይደርስ፣ የማያዋጣ የትግል ስልት የሚከተሉና ፣ፀረ ሕዝብ አመለካከት ያላቸው ፣ ሕዝባቸውን በመዝረፍ ሀብት ማካበት የሚሹ መሆናቸው ላይ የቦረና ሕዝብ መግባባት አለበት” ብለዋል፡፡

መንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አድርጓል አሁንም የሰላም አማራጭ የሚፈልጉ ካሉ ለመቀበል ዝግጁ ነው ያሉት አቶ አሊ በየአካባቢው ያሉ ታጣቂዎች አሁንም ሰላምን መርጠው እንዲገቡ ልጆቻችሁን መክራችሁ አምጡና ቦረና ሰላም ይስፈንበት ነው ያሉት፡፡
ከአርሶ አደር መሳሪያ መቀማት ጀግንነት አይደለም

ይህ የዘራፊዎች ስብስብ በወረዳው ሕዝብ ውስጥ የማያቀባብር ነውረኛ ተግባር እየተሠራ እንደሆነ መገንዘብ አለባችሁ ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ በርካታ ምሁራን የሚፈልቁባቸው የቦረና ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው እንደሚያስቆጭም አንስተዋል። ከመንግሥትና ከፀጥታ ኀይሉ ጎን ተሰልፋችሁ ሰላማችሁን አስፍናችሁ ልጆቻችሁ ይማሩ ፣ ዩኒቨርሲቲውም ተማሪዎችን ይቀበል ፣ የመሰረተ ልማቶቹ ግንባታ ይቀጥል ፣ ሕዝቡ ትኩረቱን ወደ ልማት ያድርግ ብለዋል የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፡፡

ውይይቱ ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡

ዘጋቢ፦ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአውሮፓ ኅብረት የሚደገፍ የ2 ሚሊዮን ዩሮ የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።
Next articleጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተሉ መኾኑ ተጠቆመ።