በአማራ ክልል ተቋማት በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ ነው።

38

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የመንግሥት ተቋማት ላይ በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አስታውቋል። የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቤል ፈለቀ በክልሉ በአራት ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። መሠረተ ልማቱን ለዲጂታልና አውቶሜሽን ማመቻቸት፣ በተቋማት እና በማኅበረሰብ ወቅቱን የሚመጥን የዲጂታል እና የሳይበር ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን የተሳለጠ እንዲኾን እና በተቋማት መካከል ትስስር እንዲጠናከር የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሠራበት ነው ብለዋል።

የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ሲሠራ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ማኅበረሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን እና ክልሉ የሚፈልገውን አበርክቶ ሲሰጥ አለመቆየቱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለአደረጃጀት ትኩረት በመስጠት ፣ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ከተለያዩ አካባቢዎች በማምጣት፣ የሰው ኃይሉን የተሻለ ሥራ እንዲሠራ በማነሳሳት የሚጠበቅበትን ተግባር ለመወጣት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ተቋማት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የሚለሙ ቴክኖጂዎች ፍላጎትን የሚረዱና መሬት ላይ ያለውን ችግር የሚፈቱ መኾን አለባቸው ነው ያሉት። ሲስተም ሲለማ ተጠቃሚው አካል የመጠቀም አቅም አብሮ የልማቱ አካል እንዳልነበር ያነሱት ኮሚሽነሩ በዚህ ምክንያት የሚለሙ ቴክኖጂዎች በሚጠበቀው ልክ ውጤታማ እንደማይኾኑ ነው የተናገሩት። አሁን ላይ ተቋሙ የሚሠራቸው ሥራዎች የእስካሁን ችግሮችን የለዩና በመሠረታዊነት ችግሮችን የሚፈቱ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።

የሚለሙ ሲስተሞች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያለውን ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። የሚያለሟቸው ሲስተሞች የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን እንደሚፈቱም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአገልግሎት አሰጣጡን ከንክኪ ነጻ ለማድረግ እየተሠራ ነው” እንድሪስ አብዱ
Next article“ጣናን ተንተርሳ የተመሠረተችው ባሕር ዳር ከተማ ቱሪዝም ዋነኛ መወዳደሪያዋ ነው” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል