“የአገልግሎት አሰጣጡን ከንክኪ ነጻ ለማድረግ እየተሠራ ነው” እንድሪስ አብዱ

52

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 2/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ እና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አዲስ የበለጸገ ድረ ገጽም አስተዋውቋል። ማንኛውንም ዓይነት የክልሉን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መረጃዎች ለማግኘት (www.investinamhara.gov.et) ድረ ገጽን መጎብኘት እንደሚቻልም ተመላክቷል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ መንግሥት በትኩረት ከያዛቸው ጉዳዮች አንደኛው የተቋም ግንባታ ነው ብለዋል። የተቋም ግንባታ የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ማዘመን እና አሠራሩን ማስተካከል መኾኑን ነው ያመላከቱት። ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ጋር የሚሠሩት ሥራ የተቋሙን አሠራር ዘመናዊ ማድረግ እንደሚችልም ተናግረዋል።

በክልሉ ወጥ እና የተናበበ እቅድ አፈጻጸም እንዲኖር እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ወቅቱን የሚመጥን ክልሉን ተወዳዳሪ ማድረግ የሚችል፣ የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅም ተደራሽ ሊያደርግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በበጀት ዓመቱ ተቋሙን የማዘመን ሥራ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ቢሮው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምድ እንዳለው የተናገሩት ኀላፊው ያለውን ልምድ ተጠቅመን የአግልግሎት አሠጣጡን ከንክኪ እና ከደለላ ነጻ የማድረግ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በመግባባት ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ጋር በመኾን ድረ ገጽ ማልማታቸውንም ተናግረዋል። ክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ የኾነ ክልል መኾኑንም አስተዋውቀዋል። ያለውን ጸጋ ሌሎች እንዲያውቁት እና ኢንቨስት እንዲያደርጉበት ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።

ድረ ገጹ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀንቋዎችን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።ባለሃብቶች በራሳቸው ቋንቋ አማካኝነት ክልሉን ማስተዋወቅ ጠቃሜታው የጎላ መኾኑን አመላክተዋል። ቴክኖሎጂ ግልጽ እና ቀልጣፋ የኾነ አሠራር እንዲኖር እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቤል ፈለቀ ኮሚሽኑ ለሁሉም የክልሉ ተቋማት ሲስተም ለማልማት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የክልሉን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ፣ የፈቃድ አሰጣጡ የተሳለጠ እንዲኾን ለማድረግ እና ክልሉ በኢንቨስትመንት ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዲያገኝ የሚያስችል ሲስተሞችን እያለሙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

የተሠራው ሥራ ዘመኑን የሚመጥን እና በጥናት ላይ የተመሠረተ መኾኑን ነው የገለጹት። የተፈጥሮ ሃብትን ማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ ዲጂታላይዜሽን እና አውቶሜሽንን እውን የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ እንደ ክልል ከሚያስገኘው ጥቅም አንጻር ለኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ሰጥተናል ነው ያሉት። ለሌሎች ክልሎች እና ተቋማት አርዓያ የሚኾን ሲስተም እንደሚለማም ተናግረዋል። ኮሚሽኑ አስፈላጊውንን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ልምድ የሚቀመሰምበት ሥራ እንሠራለንም ብለዋል።

ለቢሮው የበለጸገው ድረ ገጽ ዘመናዊ፣ ብዙ መረጃዎችን የሚይዝ፣ ትስስር ያለው መኾኑን ነው የተናገሩት። በክልሉ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች እንደሚያመላክትም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት ወራት ከ940 በላይ አዳዲስ አልሚዎች ወደ አማራ ክልል መጥተዋል።
Next articleበአማራ ክልል ተቋማት በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ ነው።