ባለፉት ወራት ከ940 በላይ አዳዲስ አልሚዎች ወደ አማራ ክልል መጥተዋል።

8

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ጉዳቶች ደርሰዋል። በክልሉ የነበረው የኢንቨስትመንት ፍሰትም ፈተና ገጥሞት ቆይቷል። የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ መቆየቱን ተናግረዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ በአግባቡ የማያቀርቡበት፣ ምርታቸውን ወደ ገበያ የማያቀርቡበት፣ ባለሀብቶች በስጋት አካባቢውን ለቀው የሄዱበት እና አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ለመምጣት አስቸጋሪ የነበረበት ወቅት እንደነበር ነው ያነሱት።

አሁን ላይ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ባለፉት ወራት ከ940 በላይ አዳዲስ አልሚዎች ወደ ክልሉ መምጣታቸውንም ተናግረዋል። 93 አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች ኢንቨስትመንት እየተነቃቃ መኾኑን የሚያሳዩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ክልሉ ወደተሟላ ሰላም በሚሸጋገርበት ጊዜ የክልሉ ኢንቨስትመንት እንደሚነቃቃና አቅሙ ከፍ እንደሚል ገልጸዋል።

ሰላሙ እንዲጸና እና የተሟላ እንዲኾን ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን መወጣት እንደሚገባውም ተናግረዋል። ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም ካደገ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። አዳዲስ አልሚዎችን ወደ ክልሉ ለማምጣት እና ነባሮችን ለማቆየት የአግልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በሚቀጥሉት ጊዜያት የተሻለ ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። “አሁን ከገባንበት የጸጥታ ችግር ዋና መውጫ መንገዳችን ኢኮኖሚ ላይ መሥራት ነው” ብለዋል። ኢኮኖሚው እንዲያድግ ደግሞ አምራች ኢንዱስትሪው እንዲነቃቃ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት። የአማራች ኢንዱስትሪው እንቅፋት እንዳይገጥመው፣ ባለሀብቶች ተስፋ ቆርጠው ከክልሉ እንዳይወጡ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የሰው ኃይል መቅጠር የሚችሉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ሕዝብን እያማረረ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመፍታት እና መሠረታዊ አቅርቦቶችን ለማሟላት የአማራች ኢንዱስትሪዎች ሚና ከፍ ያለ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ኢኮኖሚ ላይ መሥራት የሁሉ ነገር መሠረት ነው ብለዋል። አምራች ኢንዱስሪዎች በሙሉ አቅማቸው ሲሠሩ የኢኮኖሚ ሽግግር እንዲኖር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሀገሪቱ ቁልፍ ተቋማት ብሔራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ በቅንጅት ለመሥራት ስምምነት አደረጉ።
Next article“የአገልግሎት አሰጣጡን ከንክኪ ነጻ ለማድረግ እየተሠራ ነው” እንድሪስ አብዱ