የሀገሪቱ ቁልፍ ተቋማት ብሔራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ በቅንጅት ለመሥራት ስምምነት አደረጉ።

32

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዘጠኝ የሀገሪቱ ቁልፍ የመሠረተ ልማት ተቋማት የኤርፖርትና ድንበር አሥተዳደር ትራንስፎርሜሽን የመግባቢያ ሥምምነት አካሂደዋል። የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተልጄንስ ኢንስቲትዩት፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን፣ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ናቸው።

የሥምምነቱ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ከ5 ሺህ 383 ኪ.ሜ በላይ የሚረዝም ድንበር ያላት በመሆኑ ድንበር ላይ የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት እና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት የሚጎዱ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በየብስ፣ በባቡር፣ በአየር፣ በባሕር እና በስፔስ ተቋማት መረጃን በመለዋወጥ ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው።

ሥምምነቱ ዓለምን እየፈተነ የሚገኘውን የሳይቀር ጥቃት እና ድንበር ተሻጋሪ ወረርሽኞችን በጋራ ለመከላከል ፋይዳው የላቀ ነው ተብሏል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሐሚድ የመግባቢያ ሥምምነቱ ብሔራዊ ደህንነትን ለማስከበር፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቀ፣ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል ፣ የሳይበር ደኅንነት አቅምን ለማጎልበት፣ በቴክኖሎጂ ለመታጠቅ፣ የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ፣ ብቁ የሰው ኀይል ለማፍራት እንዲሁም ቁልፍ መሠረተ ልማትን ከሚያስተዳድሩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እና በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪላቬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ ቴክኖሎጅዎች በየጊዜው እየተቀያየሩና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነት እያደገ መምጣቱን አንስተው የሀገሪቱ የአቬሽን ኢንዱስትሪ በዓለማቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ተመራጭና ለደንበኞች ምቹ ለማድረግ ሥምምነቱ ወሳኝ ነው ብለዋል። የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። ከተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር እንሠራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋመስፍ ጣሰው በበኩላቸው የአየር መንገዱ በአፍሪካ ቀዳሚ ደረጃ እንደሚገኝ አንስተዋል። አየር መንገዱ የዲጅታል ሥርዓትን በመዘርጋት ታማኝነቱ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ ለደንበኞች ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እየሠጠ ነው ብለዋል። ዛሬ የተደረገው የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ስምምነት ተግባራዊ እንዲኾንም እንሠራለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ደረሰ ሕገወጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን በማስቀረት እና ንግድን በማቀላጠፍ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። በተለይም ድንበር ላይ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡና የሚወጡ ምርቶችን በቴክኖሎጅ በመደገፍ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መኾኑን አንስተዋል። ለተግባራዊ ተፈጻሚነቱም ተቋሙ በቁርጠኝነት ይሠራነን ነው ያሉት።

ዘጠኙም የሀገሪቱ ቁልፍ ተቋማት የሀገርን ብሔራዊ ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በቅንጅትና በትብብር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን እየተመለከቱ ነው።
Next articleባለፉት ወራት ከ940 በላይ አዳዲስ አልሚዎች ወደ አማራ ክልል መጥተዋል።