
ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ባለው 21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን የማጠቃለያ መድረክ ነው። የጸረ-ሙስና ትግልን ውጤታማ አድርጎ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ለምናደርገው ጥረት እና ለዚህ መሻታችን ሥነ ምግባር እና ሥርዓትን አስማማተው የያዙ ወጣቶች ሊኖሩን ይገባል ብለዋል።
ሙስናን ለመከላከል እና ለማጥፋት ብዙ ሥራዎች ቢሠሩም ከታሰብው ግብ አልደረሰም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በወጣቶች ላይ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። ለዚህ ደግሞ የመጪው ጊዜ ቃል ኪዳን በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ተዘጋጅቶ የጸደቀ ስምምነት መኖሩን አስታውሰው፤ የዚህ ስምምነት ዋና ግብ በፀረ-ሙስና ትግል ወጣቶችን ማሳተፍ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም ተቋማዊ አሠራርን ማጽናት፣ የተቋማትን መናበበ እውን በማድረግ እና በትምህርት ተቋማት የሞራል እና ግብረ ገብ ትምህርት በመስጠት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል። ሙስና ለረጅም ጊዜ ያቆየናቸውን ማኅበራዊ ወረቶችን ሁሉ የሚያሽመደመድ፣ እድገትን የሚሰብር እና የነገውን ትውልድ ጥሪት የሚያሟጥጥ በሽታ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ይህንን በሽታ ሃሳባዊም ባሕላዊም ሽፋን እየሰጠነው እንዳንጠየፈው አድርገነው ቆይተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ በሽታ የተለከፉ ሰዎች በሽታውን እንደካባ ለብሰው ለመንቀሳቀስ አያፍሩም ብለዋል። እንዲህ ያለውን በሽታ ለማጥፋት የወጣቱን ሥነ ምግባር በሚገነቡ የሚዲያ ሥራዎች በማገዝ የተቀናጀ ሥራ መስራት እንደሚገባም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ፣ በኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ የምክር ቤት አባላት፣ የፌደራል የሥነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ.ር)፣ ሚኒስትሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ዛሬ የማጠቃለያ መድረኩ እየተካሄደ ያለው 21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ-ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል” በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል።